ሚያዚያ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-
የትንሳኤ በአልን ምክንያት በማድረግ በእስር ላይ የሚገኙትን የህሊና እስረኞች ለመጠየቅ ወደ ቃሊቲ ያመሩት የአንድነት ፓርቲ አመራሮች እስካፍንጫቸው በታጠቁ ልዩ ሀይሎች በግድ ከአካባቢው እንዲርቁ መደረጉን ፍኖተ ነጻነት ዘገበ
ወጣቱን ፖለቲከኛና ከፍተኛ አመራር አንዱአለም አራጌና ናትናኤል መኮንን ሽብርተኞች እንደሆኑና በሰላማዊ ትግል ሽፋን ሽብርተኝነትን እንደሚያራምዱ ተደርጎ የቀረበው ሀተታና ውሳኔ እጅግ ያሳዘናቸው በርካታ አመራሮችና አባላቱ በከፍተኛ መነሳሳትና ቁጭት ከ 20 በላይ የሚሆኑ የፓርቲው ሰዎች ከ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ እንኳን አደረሳችሁ ለማለት ቢገኙም የተሰጣቸው ምላሽ አንዷለምን ምግብ ከሚያመላልሱለት ጥቂት ቤተሰቦቹ ውጭ ማንም እንደማይጠይቀው ተነግሮአቸዋል።
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ዶ/ር ያዕቆብ ሀይለማርያም፣ አቶ አክሉ ግርግሬ፣ አቶ ሙላት ጣሰው፣ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን፣ አቶ ተክሌ በቀለ፣ አቶ ትዕግስቱ አወሉ፣ አቶ ዳንኤል ተፈራና ሌሎችም የፓርቲው አመራሮች በልዩ ሀይሎች ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርገዋል።
ከዚህ በፊት በተለይ አንዷለም አራጌን ከጥቂት ቤተሰቦቹ በስተቀር ማንም እንዳይጠይቀው የተደረገ ሲሆን በተደጋጋሚ አመልክቶ ምንም ምላሽ እንዳላገኘ ጋዜጣው ዘግቧል።
ከወትሮው በተለየ ሁኔታ አካባቢውን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች መውረራቸውን በፎቶ ግራፍ አስደግፎ የዘገበው ጋዜጣው ፣ ለመጠየቅ የመጡት ሰዎች መጠየቅ መብታቸው እንደሆነ ለማስረዳት ቢሞክሩም ልዩ ሃይሎች መሳሪያቸውን በተጠንቀቅ በመያዝ ፀብ ለማስነሳት ሙከራ ማድረጋቸውም ተገልጿል።
በሌላ በኩል ደግሞ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን የተዛባ ፍርድ አስመልክቶ ከቃሊቲ በጻፈው ጽሁፍ ዲሞክራሲ ዋጋ የሚያስከፍልና ውጣ ውረድ የበዛበት መንገድ ያለው መሆኑን ገልጾ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ ዘግይቶም ወይም ፈጥኖ ይመጣል ብሎአል። እስክንድር ማንኛውንም መስዋትነት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን እና በዚህ አቋሙ እንደሚጸናም ተናግሯል። የልጁ ናፍቆት ከሚችለው በላይ እንደሆነበት ያልሸሸገው እስክንድር ፣ ዲሞክራሲ በአገራችን ሰፍኖ እንደሚያይ እምነቱን ገልጿል።