በዜጐች መፈናቀልና እንግልት ላይ ተሣታፊ የሆኑ የመንግስት ሀላፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ እንቅስቃሴ ተጀመረ

ሚያዚያ ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የዜጐችን መፈናቀል ለማስቆምና በዜጐች መፈናቀልና እንግልት ላይ ተሣታፊ የሆኑ የመንግስት ሀላፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚያግዝ ፒቲሽን ለማስፈረም እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ፓርቲው፤ኢትዮጵያዊ ምሁራን የሚሣተፉበትና መፈናቀሉ እያስከተለ ባለው ጉዳት ዙሪያ በመወያየት የመፍትሄ ሀሣብ የሚመነጭበት አገር አቀፍ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድም ገልጿል፡፡

አዲስ አድማስ የፓርቲው ን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊና የኤዲቶሪያል ቦርድ አባል አቶ ዳንኤል ተፈራን በመጥቀስ እንደዘገበው፤ አንድነት ፓርቲ፤ እየተካሄደ ያለው ዜጐችን የማፈናቀል ተግባር አገር አቀፍ ይዘት ያለው መሆኑን ያምናል፡፡

ይህን አገር አቀፍ ማፈናቀልና እንግልት ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስቆም ፓርቲው ፒቲሺን ለማሠባሠብ መዘጋጀቱን የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ ይህን ተግባር ለማከናወን በፓርቲው የፖለቲካ ጉዳይ የበላይ መሪነት አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ መዋቀሩንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም፤ህዝቡ እና- ይህ ህገ-ወጥ ተግባር እንዲቆም የሚፈልግ የትኛውም አካል፤ ፊርማውን በማኖርተቃውሞውን እንዲገልፅ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የፊርማ ማሠባሠቡ ሥራ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ እንደሚከናወን የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ ከዚያ በኋላ ፓርቲው -ከህግ ክፍሉ ጋር በመመካከር ጉዳዩን ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለም ፍ/ቤቶች
እንደሚያቀርበው ተናግረዋል፡፡
በተመሣሳይ በጉዳዩ ዙሪያ አገር አቀፍ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ የገለጹት አቶ
ዳንኤል ፤ ውይይቱ በዋናነት የሚያተኩረው ዘርን መሠረት አድርገው የሚፈፀሙ መፈናቀሎች
የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነትና ሠላም የሚያፈራርሱ መሆናቸውን ማሳየት ላይ ነው።

በመሆኑም፣ ኢትዮጵያዊ ምሁራን በውይይቱ በመሣተፍ፣ የመፍትሄ ሀሣብ በማምጣትና ህዝቡን
በማስተማር ዜጐችን የመታደግ ሀላፊነት እንዳለባቸው አቶ ዳንኤል አሣስበዋል።