ህዳር 21 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ዝቅተኛው አርሶአደር ለአባይ ግድብ ማሰሪያ 500 ብር እንዲያወጣ፣ ለህዝብ ማመላለሻ መኪና ክላውዲዮ የሚያወጡ ደግሞ 7 ሺ ብር እንዲከፍሉ እንዲሁም መምሀራን የደሞዛቸውን 100 ፐርሰንት እንዲከፍሉ የሚያደርግ መመሪያ ወጣ ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ዝቅተኛ የተባለው ገበሬ ለግድቡ ማሰሪያ አምስት መቶ ብር እንዲያዋጣ፣ የተሻለ ገቢ አለው የተባለው ገበሬ ደግሞ ከ1 ሺ ብር ጀምሮ እንደዬደረጃው እንዲከፍል ይደረጋል።
የወረዳ ባለስልጣናት ይህን መመሪያ እንዲያስፈጽሙ ትእዛዝ የተሰጣቸው ሲሆን፣ እርምጃቸው ገበሬውን ለተቃውሞ ሊያነሳሳው ይችላል በሚል ስጋት ፣ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት አላቸው የሚባሉትን ሽማግሌዎች መርጦ የማሳመን ስራ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች መምህራን “ለግድቡ ግንባታ ገንዘብ በውዴታ እንጅ በግዴታ አንከፍልም” የሚል ተቃውሞ ማስነሳታቸውን ተከትሎ መንግስት በፈለጉት መጠን እንዲያዋጡ ውሳኔ አስተላልፎ ቢቆይም፣ አሁን ግን ውሳኔው ተሽሮ እያንዳንዱ መምህር የአንድ ወር ሙሉ ደሞዙን እንዲያዋጣ መመሪያ መተላለፉ ታውቋል።
በህዝብ ትራንስፖርት ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የመኪና ክላውዲዮ ለመቀዬር ደግሞ በነፍስ ወከፍ 7 ሺ ብር መክፈል ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ውሳኔውን የሰሙ አንዳንድ ባለ ንብረቶች በንብረታችን ማዘዝ የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል በማለት ሲያማርሩ መሰማታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
መኪናቸውን ለመሸጥ የሚፈልጉት የህዝብ ትራንሰፖርት ባለንብረቶች ፣ መኪናቸውን ሲሸጡም ለአባይ ግድብ ማሰሪያ 7 ሺ ብር ከፍለው ክላውዲዮ አስለጥፈው መሸጥ ግድ ይላቸዋል።
መንግስት በአባይ ግንባታ ስም ህዝቡን በእጅጉ እንዲማረር ማድረጉን ተከትሎ ደራሲ እና ሀያሲ አለማየሁ ገላጋይ “ለደሀ አገር የት ነው? ተቆርቋሪውስ ማን ነው?’ በሚል ርእስ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ባሰፈረው ጽሁፉ ” ከእንዲህ ያለ ሮሮ በስተጀርባ ያለ ልማት እንዴት ያለ ነው? ከገዛ ስጋ መዋጮ እንዲደረግለት የታሰበው የሰማየ-ሰማያት ጉዞ የት ያደርሰናል? ህዝብ ድንበር ጥሶ እየፈለሰ ውሃን ገድቦ ለማስቀረት መውተርተር ምን ይሉት
ህልም ነው? የግብፆቹ ፈርዖኖች በባሮቻቸው ላይ የፈፀሙት ከሰው ግንባታን የማስቀደም ስህተት እኛን የት ያደርሰናል? ለመሆኑ ለድሃ ሀገሩ የት ነው? ተቆርቋሪውስ ማነው? ” በማለት በኢትዮጵያ ያለውን የህዝብ ብሶት ገልጧል።
መንግስት የአባይን ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ በማድረግ አገኘዋለሁ ብሎ ያሰበው ገንዘብ እንደተፈለገው አለመገኘቱ በእጅጉ እንዳሳሰበው መረጃዎች ያሳያሉ።