የኦክላንድ የምርምር ተቋም በኢትዮጵያ የሚደረገው የመሬት ሽያጭ መቆም እንዳለበት ገለጠ

ህዳር 21 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-ታዋቂው የኦክላንድ የምርምር ተቋም በኢትዮጵያ የሚደረገው የመሬት ሽያጭ መቆም እንዳለበት ገለጠ፣ በጋምቤላ መሬት የሚወስዱትና ንግዱን የተቆጣጠሩት የአንድ ብሄር ሰዎች መሆናቸውንም አጋለጠ ተቀማጭነቱ በካሊፎርኒያ አሜሪካ የሆነው የኦክላንድ የምርምር ተቋም መስራችና የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አኑራዳ ሚታል ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጡት ፣ የኢትዮጵያ መንግስት እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ እና ህገወጥ በሆነ መንገድ የሚቸበችበው መሬት፣ ለአገሪቱ አደገኛ ሁኔታን የሚያስከትል በመሆኑ ሊቆም ይገባዋል።

የመሬት ሽያጩ በአካባቢው ነዋሪ ላይ ከፍተኛ የሆነ ስቃይ እያመጣ መሆኑን ዳይሬክተሯ ተናግረው፣ ህዝቡ በበቂ ሁኔታ ሳይመክርበት የሚደረገው ሽያጭ ህገወጥ ነው ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

ሚታል ሲናገሩ፣ ” መንግስት የውጭ  አገር ኩባንያዎች ለሚወስዱት ለም መሬት የሚያስከፍለው ገንዘብ መጠን ሲታይ በጣም የሚያስደነግጥ ነው፤ በዚያ ላይ ስምምነቶች በአካባቢ ላይ ስለሚያመጡት ተጽእኖ የሚናገሩት ነገር ዬለም።”

የመለስ መንግስት “መሬትን ለውጭ አገር ባለሀብቶች መቸብቸብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላል” የሚለውን መከራከሪያ እንደማይቀበሉት የገለጡት ባለስልጣኑዋ፣ እንዲያውም ድርጊቱ  በአገሪቱ ያለውን ረሀብ  ሊያባብሰው ይችላል በማለት ስጋታቸውን ይገልጣሉ።

“ኢትዮጵያ ውስጥ 13 ሚሊዮን ህዝብ በምግብ እርዳታ እንደሚኖር እናያለን፤ እህል የጫኑ የእርዳታ መኪኖች ወደ አገሪቱ ሲገቡ እንመለከታለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ እህል፣ አበቦችንና የቅባት እህሎች የጫኑ መኪኖች አገሪቱን ለቀው ሲሄዱ እንመለከታል። ኢትዮጵያ ማለት በእንዲህ አይነት መስቀለኛ መንገድ የምትገኝ አገር ናት።” ሲሉ ዳይሬክተሩዋ አክለዋል።

አሁን እየተካሄደ ያለው የመሬት ሽያጭ አነስተኛ ገበሬዎችን የማያበረታታ በመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ እንዲስፋፋ እንደሚያደርገው ሚታል ይናገራሉ።

ዳይሬክተሩዋ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ደሀ አርሶአደሮችን ከመሬታቸው በጉልበት እያፈናቀለ መገኘቱንም ነቅፈዋል።

ተቋሙ በጋምቤላ ስላለው የመሬት ይዞታ ባወጣው ዘገባ ፣  በክልሉ ውስጥ አብዛኛውን መሬት የያዙት የትግራይ ብሄር ተወላጅ የሆኑ የስርአቱ ደጋፊዎች መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ሰዎችም ከሰል እያከሰሉ ከመሸጥ ውጭ የረባ ስራ አንደማይሰሩ አመልክቷል።

የገዢው ፓርቲ ደጋፊ የትግራይ ተወላጆች መሬት በቀላሉ እንደሚያገኙ፣ የባንክ ብድር እንደሚመቻችላቸውና በክልሉ ዋነኞቹ አዘዦች እንደሆኑ ተመልክቷል።

ገዢው ፓርቲ ይህን የሚያደርገው በጠረፋማ አካባቢዎች ያለውን ህዝብ ለመቆጣጠር እንዲያመቸው መሆኑም ተገልጧል።