ወጣት ብሌን መስፍን በድጋሜ ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጣት

ጥቅምት ፲፯ (አሥራ ሳባት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከሕግ አግባብ ውጪ ተይዛ በስቃይ ላይ የምትገኘው የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነችው ወጣት ብሌን መስፍን በአስር ሽህ ብር ዋስትና መብቷ ተፈቅዶላት ውጪ ሆና ጉዳይዋን እንድትከታተል ሲል የሰባራ ባቡሩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወቅቱ ውሳኔ ቢያሳልፍም፣ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም አቃቤ ሕግ ባቀረበው ይግባኝ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው የክስ መቃወሚያ ጉዳዩን የሚያየው ኮማንድ ፖስቱ በመሆኑ በእስር ላይ ትቆይ ብሎአል። የብሌን ጠበቃ በበኩላቸው በደንበኛቸው ላይ የቀረበባት ክስ ከህግ አግባብ ውጪ እንደሆነና ብሌን መስፍን የተያዘችበት ቀን መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም ሲሆን ይህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ በፊት በመሆኑ፣ የኮማንድ ፖስቱ አዋጅ ጉዳይ አይመለከታትም ሲሉ ተከራክረዋል። ፍርድ ቤቱም በውሳኔው ላይ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።