ሶማሊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር መካከል ያለው አለመግባባት እየጨመረ ነው

ጥቅምት ፲፯ (አሥራ ሳባት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ስር በሚገኘውና ከሰላም አስከባሪው ውጭ በሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ጦር መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ በመሄዱ ጦሩ በተለያዩ ጊዜያት እርስ በርስ ተዋግቶ የበርካታ ወታደሮች ህይወት ማለፉን ምንጮች ገልጸዋል።

በአሚሶም ስር ያሉ ወታደሮች ክፍያ የሚያገኙት ከአለማቀፍ ለጋሾች ከሚሰበሰበው ዶላር ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ ከአሚሶም እውቅና ውጭ ያስገባቸው የጦሩ አባላት ግን ክፍያ የሚሰጣቸው ከመንግስት ባጀት ወጪ ተደርጎ በብር ነው። ከአሚሶም እውቅና ውጭ የሚገኙት በአሚሶም ስም ያሉትን ወታደሮች እንዲጠብቁ ተብሎ ቢሆንም፣ አሚሶም ግን ለእነዚህ ወታደሮች እውቅና አልሰጥም በማለቱ በአሚሶም እና በኢህአዴግ መንግስት መካከል ውዝግብ ሲነሳ ቆይቷል። ከአሚሶም ውጭ የሚንቀሳቀሱ ከ4 ሺ በላይ የሚሆኑ የሰራዊቱ አባላት ፣ እኛ ደማችንን እያፈሰስን፣ ገንዘቡን የሚወስዱት ግን ሌሎች ናቸው” በሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፣ እስከዛሬ በቂ መልስ ሳይሰጣቸው ቆይቷል። ችግሩ እየሰፋ ሄዶ በአሚሶም ስር በሚገኙትና ከአሚሶም ውጭ በሚንቀሳቀሱት ወታደሮች መካከል በተደጋጋሚ ግጭት የተፈጠረ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ግጭቱ የፖለቲካ ቅርጽ ይዞ ቀጥሎአል።

የኦሮምያና የአማራ ተወላጅ ወታደሮች በህወሃት አባላት አዛዦች ላይ ማመጽ የጀመሩ ሲሆን፣ ከአሚሶም ውጭ የሚንቀሳቀሰውን ጦር የሚመሩ አዛዦች መገደላቸው ታውቋል። ችግሩ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ፣ ገዢው ፓርቲ ከአሚሶም ውጭ የሆነውን ሰራዊት ከሶማሊያ እያስወጣ ሲሆን፣ አልሸባብም የሚለቀቁትን ቦታዎች በፍጥነት  በቁጥጥሩ ስር እያዋለ ነው።

የኢትዮጵያ ጦር የመረጃ ሰራተኞች ሚስጢር በአልሸባብ እጅ መውደቁን ተከትሎ በኢትዮጵያ የአሚሶም ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ፣ ጥቃቱን ለመሸፋፈን በሚል ፣ ጄ/ል ሳሞራ የኑስ 4 ሺ የሚሆን ከአሚሶም ውጭ የሆነ ጦር ወደ ሶማሊያ እንዲገባ ከአመታት በፊት አዘው ነበር።

በወታደሮች መካከል ያለው አለመግባባት መጨመር በአገሪቱ ውስጥ እየተባባሰ ከመጣው አመጽ ጋር ተደማምሮ ፣ በአሚሶም ስር ያልሆነውን ሰራዊት በማስወጣት በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች እያሰፈረ ይገኛል። ሰራዊት የማስወጣቱ እንቅስቃሴ የዛሬ ሁለት ወር በፊት ገደማ መጀመሩን ኢሳት ዘግቦ ነበር።

ከአሚሶም እውቅና ውጭ ሰራዊት ማስገባቱን ያልገለጸው የኢህአዴግ አገዛዝ፣ሰራዊቱን ማስወጣቱን ተከትሎ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ጌታቸው ረዳ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ፣ ያስወጣነው በአሚሶም ስር ያልታቀፈውን ነው በማለት ሰራዊት ማስገባታቸውን ማረጋገጫ  ሰጥተዋል።