ወደ ኬንያ የተሰደዱ በሺህዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሞያሌ ነዋሪዎች በወታደሮች የደረሰባቸውን ግፍ ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 05 ቀን 2010 ዓ/ም) እንደ ኬንያው ኔሽን ዘገባ ከ8ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ትናንት ማክሰኞ ማርሳቢት ተብላ በምትጠራው የኬንያ ከተማ የገቡ ሲሆን፣ ከመኖሪያ ቤታቸው ተገደው እንዲወጡ መደረግን ጨምሮ በወታደሮች የተፈጸመባቸውን ግፍ ተናግረዋል።
መንግስታቸው በንጹሀን ዜጎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ በመጀመሩ ሀገራቸውን ለመልቀቅ መገደዳቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ኮማንድ ፖስቱ ያሰማራቸው ታጣቂዎች ባለፈው ቅዳሜው በሞያሌ 13 ንጹሀን ዜጎችን መግደላቸው ይታወቃል።
የዜና አውታሩ እንዳለው፣ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ ዜጎቹን የመጠበቅ ኃላፊነትን ባለመወጣት መንግስታቸውን ይከሳሉ። 8ሺህ 200 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኬንያ ኖያሌ ቡቲዬ ውስጥ በሚገኝና መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት በሚተዳደር ማህበራዊ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ነው የሰፈሩት።
መጠለያው ያረፈበት ስፍራ ንብረትነቱ የማርሳቢት ገዥ የሆኑት የአቶ ማህሙድ መሀመደ እና የዳምባላ ፋቻና ነው።
የ19 ልጆች አባት የሆኑት የ68 ዓመቱ አዛውንት አቶ ሃርሳሜ ሃላኬ ፣ ወታደሮቹ ቤታቸውን በመውረር እንዲተኙ ካዘዟቸው በኋላ ጥይት በመተኮስ የተወሰኑትን እንደገደሏቸው ለኔሽን ተናግረዋል።
“እንደ መስጊድ ያሉ የአምልኮ ቦታዎች ሳይቀሩ የግድያ ቀጣናዎች ሆኑ።ሰዎች በመስጊድ ሲገደሉ በዓይኔ ተመልክቻለሁ።ለጥቂት ነው ከሞት አምልጬ ከህጻናትና ከግመሎች ጋር የተሰደድኩት”ሲሉም አክለዋል አዛውንቱ።የ18 ዓመቷ ወጣት ካሹሬ ጉዮ ደግሞ ከኢትዮ ኬንያ ድንበር 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና” ሻዋ ባሬ”በምትባለው ከተማ ወታደሮች እንደደበደቧቸው ተናግራለች።
“ወታደሮቹ ድንበር አቋርጦ የሚመጣን ማናቸውንም ሰው እየተኮሱ ይገድሉ ነበር”ስትልም ወጣት ካሹሬ አክላለች።እሷም በምታመልጥበት ጊዜ እጅና እግሯን ተመትታ መቁሰሏን ለጋዜጠኞች አሳይታለች።
“ወታደሮቹ ወደ ገበያ ሳይቀር በመምጣት ሕዝብ ላይ ተኩስ ከፈቱ። በዙሪያችንና በላያችን ጥይት እያፏጨብን ነው ህይወታችንን ለማትረፍ ያመለጥነው” ስትልም በገበያ መሀል በሰላማውያን ህዝብ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ገልጻለች:።.
ሌሎችም በርካታ ስደተኞች በታጣቂዎች የተፈጸመባቸውን ግፍ በዝርዝር መናገራቸውን ኔሽን ዘግቧል።
የኦሮምያ ክልል ፍትህ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደዓ ግድያው በተሳሳተ መረጃ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል። ግድያው የተፈጸመባቸው ሰዎች ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ያልያዙ መሆናቸው፣ ከወደቁ በሁዋላም በጥይት መደብደባቸው ሆን ተብሎ የተፈጸመ እንጅ በስህተት ነው ብለው እንደማያሙ አቶ ታዬ ተናግረዋል። በከተማው ምንም አይነት ተቃውሞ ያልነበረ በመሆኑ እና ድርጊቱም ቀን ላይ የተፈጸመ በመሆኑ እርምጃው በስህተት ተወስዷል ብሎ መናገር እንደማይቻል ባለስልጣኑ ገልጸዋል።
የኦሮምያ ክልል አስተዳደር ወታደሮች በንጹሃን ዜጎች ላይ የወሰዱትን እርምጃ በተመለከተ እስካሁን መግለጫ አልሰጠም።