ሚያዚያ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ቁጥራቸው ከ5 ሺ በላይ የሚጠጉ ከፍኖተሰላም ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እንዲመለሱ የተደረጉት የአማራ ተወላጆች በሚመለሱበት ቦታ የደህንነት ዋስትና እንደሌላቸው ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች ገለጹ። የክልሉ መንግስት በበኩሉ ስህተት መፈጠሩን በማመን ችግሩን የፈጠሩት ታች ያሉ አመራሮች ናቸው ብሎአል።
ትናንት ማክሰኞ 21 መኪኖች፣ በዛሬው እለት ደግሞ 14 መኪኖች ተፈናቃዮችን ከአቅማቸው በላይ በመጫን ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ አቅንተዋል። የክልሉ መንግስት ፕሬዚዳንት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለጹት ተፈናቃዮች እንዲወጡ የተደረገው በስህተት መሆኑን ተናግረው ይቅርታ ጠይቀዋል። ፕሬዚዳንቱ የዞንና የወረዳ አመራሮችን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፣ እርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ተናግረዋል።
” እርምጃ ይወሰድባቸዋል የተባሉት የከማሸ ዞን አስተዳዳሪ እና የያሶ ወረዳ አስተዳዳሪ “የአካባቢውን ተወላጆች አማራ ወረራችሁ ተነሱ እያሉና እየሰበኩ ወደጫካ መግባታቸውን የደረሰን መረጃ የሚያመለክት ሲሆን የፌደራል ፖሊሶችም የሸፈቱትን ባለስልጣናት በመፈለግ ላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ሁለቱ ባለስልጣናት ስለመሸፈታቸው ኢሳት እስካሁን ከገለልተኛ ወገን ለማረጋገጥ አልቻለም።
በከማሺ ዞን በአንድ የግብርና ኢንቨስትመንት ስራ ውስጥ ተቀጥረው እስካሁን ያልተፈናቀሉ የአማራ ተወላጅ እንደገለጹት በክልሉ እየተነዛ ያለው ወሬ አደገኛ በመሆኑ ተፈናቃዮች ሲመለሱ ችግር ሊደርስባቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል
ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በመተከል ከተማ ቁጥራቸው ከ4 እስከ 5 ሺ የሚጠጉ ተፈናቃዮች የተቃውሞ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ መንግስት የተዘረፉ ንብረቶቻቸው እንዲመለሱላቸው እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
አብዛኛው የከተማው ነዋሪዎች ድጋፋቸውን ለተፈናቃዮች ሲያሳዩ እንደነበር ከስፍራው የደረስን መረጃ ያመለክታል።