የአዲስ አበባ የኢህአዴግ ደጋፊ ሴቶች ቃለ ማህላ ፈጸሙ

ሚያዚያ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሴቶች ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት ኢህአዴግን እንደሚመርጡ አስታውቀዋል

ኢህአዴግ ያለጠንካራ ተቃዋሚ በሚሮጥበት የአዲስ አበባ እና የክልል ምርጫ በአዲስ አበባ ሴቶች ሊግ አማካኝነት የቤት ለቤት ቅስቀሳ እና ማስፈራሪያ ሲደረግ ቆይቷል።

ሴቶቹ በነፍስ ወከፍ ኮፍያ እና ቲሸርት የታደላቸው ሲሆን አንዳንዶቸች አበል እንደተከፈላቸውም ለዘጋቢያችን ተናግረዋል። በተለያዩ መኪኖች ላይ ቅስቀሳ ያደርጉ የነበሩ ሴቶች የአቶ መለስ ዜናዊን ፎቶ የያዙ ቲሽርቶችን በመልበስ እንዲሁም ፎቶግራፋቸውን በመያዝ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ሴቶቹ እጅ ለእጅ በመያያዝ አቶ መለስን ራእይ እናሳካለን በማለት ቃል መግባታቸው ታውቋል።

አንድ አስተያየት ሰጪ የምርጫ ቅስቀሳው አቶ መለስ ዜናዊ ከሞት ተነስተው ለምርጫ እየተወዳደሩ ነው እንዴ ያስብላል ብሎአል። የምርጫ ቅስቀሳው ኢህአዴግን ምረጡ ሳይሆን መለስን ምረጡ ሆኗል ብሎአል።

ኢህአዴግ በ2002 የተደረገውን አገራዊ ምርጫ በ99 ነጥብ 6 በመቶ ድምጽ ማሸነፉ ይታወሳል። የሚቀጥለውን ሳምንት ምርጫም አሀዙን በነጥብ ሶስት በማሳደግ፣ በ99 ነጥብ 9 ያሸንፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዚጋቢያችን ገልጿል።