ወደየመን ሊሻገሩ የነበሩ 46 ኢትዮጵያውያን ሞቱ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 30/2010) በባህር ወደየመን ሊሻገሩ የነበሩ 46 ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ተገለጸ።

ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም ትላንት እንዳስታወቀው 100 ሰዎችን ጭና ትጓዝ የነበረች ጀልባ በመስጠሟ ምክንያት አደጋው የደረሰ ሲሆን በሕይወት የተገኙት 38 መሆናቸው ተገልጿል።

16 ሰዎች እስካሁን እንዳልተገኙ ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል።

ጀልባዋ የጫነችው በሙሉ ኢትዮጵያውያንን ነበረ። ከትላንት በስትያ መነሻዋን ከቦሳሶ ወደብ ያደረገችው ጀልባ አንድ መቶ ኢትዮጵያውያንን አሳፍራ በመጓዝ የየመን የባህር ዳርቻ ለመድረስ ተቃርባ ነበር።

እንደብዙዎቹ የስደተኛ ጀልባዎች የመስመጥ አደጋ ሊገጥማት እንደሚችል ስጋት እንደነበራቸው በህይወት የተረፉት ኢትዮጵያውያን ለአይ ኦ ኤም ገልጸዋል።

የፈሩትም አልቀረም። ጦርነት ወደሚያምሳት የመን ለመድረስ የተቃረበችው ጀልባ ከአቅም በላይ በመጫኗ ምክንያት የመስመጥ አደጋ ገጠማት።

የህይወት አድን ሰራተኞች እንደሚሉት መረጃው እንደደረሳቸው ባደረጉት ጥረት በህይወት ማትረፍ የቻሉት 38 ኢትዮጵያውያንን ብቻ ነው።

የ46 ኢትዮጵያውያን አስክሬን ወዲያውኑ የተገኘ ሲሆን 16ቱ በህይወት ይኑሩ ይሙቱ የታወቀ ነገር የለም።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም ትላንት በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ከአቅም በላይ የጫነችው ጀልባ የሰጠመችው ትላንት ጠዋት ነው።

አደገኛ በሆነው የባህር ጉዞ የተሳፈሩት ኢትዮጵያውያኑ የህይወት አድን ጃኬትም ሆነ አስፈላጊው የጉዞ ጥንቃቄ  አልተደረገላቸውም።

በህይወት የተረፉት ኢትዮጵያውያን እንዳሉት ከሀገር የወጡት በየመንና በሌሎች የአረብ ሀገራት ስራ ለመፈለግና ህይወታቸውን ለመለወጥ አስበው ነው።

ሆኖም ካሰቡበት ሳይደርሱ አብዛኞቹን መንገድ ላይ አስቀርቷቸዋል። አይ ኦ ኤም በሪፖርቱ እንዳመለከተው ከሞቱት 46ቱ ኢትዮጵያውያን መካከል 37 ወንዶች ሲሆኑ 8ቱ ሴቶች ናቸው።

የጠፉት 16ቱ ኢትዮጵያውያንም ሳይሞቱ እንደማይቀር ነው አይ ኦ ኤም በሪፖርቱ ያመለከተው።

ፍለጋው የቀጠለ በመሆኑ በመጪዎቹ ቀናት የጠፉት ኢትዮጵያውያን በህይወት መኖር አለመኖራቸው ሊታወቅ እንደሚችልም አይ ኦ ኤም አስታውቋል።

የድርጅቱ ባለስልጣን ሞሀመድ አብዲከር ለቢቢሲ እንደተናገሩት በየወሩ 7ሺህ በየዓመቱ ደግሞ 100 ሺህ ስደተኞች አደገኛውን የባህር ላይ ጉዞ በማድረግ ህይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ።

ወደ የመንና ሌሎች ሀገራት የሚደረገው ፍልሰት በአብዛኛው ከፍተኛ የሰው ልጅ እልቂት እያስተለ መቀጠሉን መረጃው ያመለክታል።

በተለይም ከምስራቅ አፍሪካ የሚሰደደው ሰው ቁጥር በከፍተኛ መጠን በመጨመር ላይ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቀዋል።

ትላንት በኢትዮጵያውያኑ ላይ ስለደረሰው ዕልቂት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም።