(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 12/2010)
ባለፈው ዓርብ ክሳቸው ተቋርጦ የነበረው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከእስር ተፈቱ።
ለኮሎኔል ደመቀ አቀባበል ለማድረግ የተዘጋጀው የጎንደር ህዝብ ከአገዛዙ ታጣቂዎች ጋር መፋጠጡንም የደረሰኝ መረጃ አመልክቷል።
ወጣት ንግስት ይርጋ ክሷ ተቋርጦ እንድትፈታ የተወሰነ ቢሆንም ከእስር ቤት እንዳልወጣች ለማወቅ ተችሏል።
በተመሳሳይ እነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ክሳቸው እንዲቋረጥ ቢደረግም እስካሁን እንዳልተፈቱ ታውቋል።
በሌላ በኩል በሽብርተኝነት ተከሰው በማዕከላዊ ከፍተኛ ስቃይ ሲደርስባቸው የነበሩት የዋልድባ መነኮሳት ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ ተወስኗል።
እስከፊታችን ረቡዕ ከእስር ይለቀቃሉም ተብሏል።
የወልቃይት ማንነት የአማራ ነው፣ ማንነታችን ይጠበቅ የሚለውን የህዝብ ጥያቄ ይዘው ውክልና ተሰቷቸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት በሽብርተኝነት ተከሰው ጎንደርና አዲስ አበባ ጉዳያቸው ሲታይ ቆይቷል።
የህዝብ ተቃውሞ እየጠነከረ መምጣቱን ተከትሎ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ ሲወሰን የኮሚቴው አባላትም ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ነጻ እንዲሆኑ ተወስኗል።
ዛሬ ከኮሚቴው አባላት አንዱ ከጎንደር መፈታታቸውን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃንም የኮሎኔል ደመቀን መፈታት በመዘገብ ለህዝብ ያስተላለፉትን መልዕክት አቅርቧል።
ኮሎኔል ደመቀ በክልሉ ቴሌቪዥን ቀርበው ለህዝባቸው ምስጋና ማቅረባቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ዘግይቶ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከእስር ወጥተው ከህዝብ ጋር ተቀላቅለዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የጎንደር ነዋሪዎች ከእስር ቤት ደጃፍ ተገኝተው ይጠብቋቸው እንደነበረ የገለጸው የኢሳት ወኪል ደስታውን ለመግለጽ በመጣው ህዝብ አካባቢው መጨናነቅ መፍጠሩን ጠቅሷል።
የአገዛዙ ታጣቂዎች ህዝቡ ለመበተን የሃይል ርምጃ መጠቀም ሲጀምር ግጭት መከሰቱን ለማወቅ ተችሏል።
ይህ ዜና በሚዘጋጅበት ሰዓት ኮሎኔል ደመቀን ለመቀበል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ወደ እስር ቤት እየጎረፈ መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ኢሳት ባለፈው ዓርብ የኮሎኔል ደመቀ ክስ እንዲቋረጥና ከእስር እንዲለቀቁ መወሰኑን መዘገቡ የሚታወስ ነው።
ከኮሎኔል ደመቀ በተጨማሪ ሌሎች አስር ሰዎች ከእስር መለቀቃቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ክሳቸው በመታየት ላይ ያሉት የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት እንዲፈቱ ተውስኗል።
ስለመፈታታቸው ግን የታወቀ ነገር የለም።
በተያያዘ ዜና በሽብርተኝነት ተከሰው በማዕከላዊ ከፍተኛ ስቃይ ሲደርስባቸው የነበሩት የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ መወሰኑ ዛሬ ተገልጿል።
አባ ገብረየሱስና አባ ገብረስላሴ የተባሉት የዋልድባ አባቶች እስከፊታችን ረቡዕ ድረስ ከእስር እንደሚለቀቁም ታውቋል።
በተመሳሳይ በጎንደር የተካሄደውን ህዝባዊ ንቅናቄ ተከትሎ በሽብርተኝነት ተከሳ በአዲስ አበባ ጉዳይዋ ሲታይ የነበረችው ወጣት ንግስት ይርጋም ክሷ ተቋርጦ እንድትፈታ ቢወሰንም እስከአሁን ከእስር ቤት እንዳልወጣች ታውቋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ፣ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌና ሌሎች ክሳቸው የተቋረጠላቸውም ሳይፈቱ ቀናት አልፏቸዋል።