በአማራ ክልል በቤት ውስጥ የመቀመጥና የስራ ማቆም አድማ ተጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 12/2010)

በአማራ ክልል ለሶስት ቀናት የተጠራው በቤት ውስጥ የመቀመጥና የስራ ማቆም አድማ ተጀመረ

በተለይም በጎንደር አድማ ሙሉ በሙሉ የተካሄደ ሲሆን ከተማዋ ከማንኛውም እንቅስቃሴ ውጭ ሆና መዋሏን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በደብረታቦር፣ በአዲስ ዘመንና በባህርዳር የአድማ እንቅስቃሴ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

የባህርዳሩን አድማ ለማስቆም የአገዛዙ ታጣቂዎች የሃይል ርምጃ እየተጠቀሙ መሆናቸው ታውቋል።

በሰሜን ጎንደር በርካታ መንገዶችም ተዘግተዋል።

በወልዲያ ተመሳሳይ የአድማ እንቅስቃሴ መኖሩ ተገልጿል።

ለስድስት ወራት የተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በሆነ ማግስት የተካሄደ አድማ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል።

የዛሬ አድማ ከዋናው ዓላማ በተጨማሪ ለአገዛዙ አፋኝ አዋጆችና ህጎች አልገዛም የሚል እምቢተኛ ህዝብ ያስተላለፈው መልዕክት ተደርጎ ተወስዷል።

በዛሬው አድማ ጎንደር ሙሉ በሙሉ ዘግታ ውላለች።

በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር እስከምሽት ድረስ የነበረውን የአድማ እንቅስቃሴ የተከታተተለው የኢሳት ወኪል እንደገለጸው በጎንደር ዛሬ የሚንቀሳቀስ ምንም ነገር አልነበረም።

ባንኮች፣ኢንሹራንሶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የንግድ ቦታዎች በሙሉ የተዘጉ ሲሆን የትራንስፖርት አገልግሎትም ተቋርጦ ውሏል።

የከተማው ከንቲባ ጠዋት ላይ በሃይለ ቃል አድማውን እንደሚያስቆሙና ርምጃ እንደሚወስዱ ሲያስጠነቅቁና ሲያስፈራሩ ከቆዩ በኋላ ምሽት በከተማዋ በሚሰራጭ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ላይ ቀርበው በልመና አድማውን እንዲያቆሙ ሲማጸኑ እንደነበር የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከጎንደር ወደ ደባርቅ፣ አርማጭሆ፣ ደብረታቦርና ሌሎች አካባቢዎች የሚያስወጡት መንገዶች በሙሉ ተዘግተዋል።

ከመተማ ጎንደርና ከሁመራ ጎንደር የሚወስዱ መንገዶችም ዝግ ናቸው።

በሰሜን ጎንደር አርማጭሆ ሙሴ ባምብ የሚወስደው መንገድም መዘጋቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

አድማውን የሚያስተባብሩ ወጣቶች ለኢሳት እንደገለጹት ለ3 ቀናት የተጠራው አድማ በጊዜያዊነት እስረኞች እንዲፈቱና ለአስቸኳይ አዋጁ አንገዛም የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ቢሆንም በዋናነት አገዛዙ ከስልጣን እንዲወርድ የተጀመረውን ትግል ለማጠናከር ነው።

ከጎንደር ሌላ ደብረታቦርና ባህርዳርም የስራማቆምና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በባህርዳር ጠዋት ላይ የተጀመረውን አድማ ለማስቆም የአገዛዙ ታጣቂዎችና የከተማዋ ባለስልጣናት እየተዘዋወሩ ለማስከፈት በወሰዱት የሃይል ርምጃ የተከፈቱ ሱቆች መኖራቸውን መረዳት ተችሏል።

በርካታ ሱቆች መታሸጋቸውም ተገልጿል።

በጋይንትና በወረታም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ መኖሩ ታውቋል።

በጎጃም ከባህርዳር በተጨማሪ በብቸና፣ በደብረወርቅና በእንጅባራ በተወሰነ ደረጃ አድማው የተካሄደ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሰሜን ወሎ በወልዲያና በአንዳንድ አካባቢዎች ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው እንደዋሉ  ከወኪላችን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።