ሁሉን አቀፍ ንግግር እንዲጀመር የአውሮፓ ህብረት አሳሰበ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 12/2010)

የኢትዮጵያ መንግስት ከሁሉም ወገኖች ጋር ሁሉን አቀፍ ንግግር እንዲጀምር የአውሮፓ ህብረት አሳሰበ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በድንገት ከስልጣን የመልቀቅ ርምጃም በሃገሪቱ ያልተጠበቁ ሁኔታዎችን መደቀኑን ህብረቱ አስታወቋል።

የአውሮፓ ህብረት ዛሬ ባሰራጨው በዚህ መግለጫ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እንደገና መታወጁም በዘላቂ መፍትሄ ጥረቱ ላይ አደጋ መደቀኑንም ገልጿል።

በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚዋቀረው መንግስት የተጀመሩ በጎ ርምጃዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሙሉ አቅም ሊኖረው እንደሚገባም አሳስቧል።

ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር የሚደረግ ንግግር ለቀውሱ ዘላቂና ሰላማዊ መፍትሄ እንደሚያመጣ የገለጸው የአውሮፓ ህብረት ባለስልጣናት፣ተቃዋሚዎች፣መገናኛ ብዙሃንና ሲቪል ሶሳይቲ መካከል ንግግር እንዲጀመርም ጥሪ አቅርቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደገና ተመልሶ መምጣቱ ዘላቂ መፍትሄ ፍለጋውን ለአደጋ ማጋለጡን ሆኖም በአጭር ጊዜ ገደብ ውስጥ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥሪ ቀርቧል።

በሃገሪቱ ሕገ መንግስት የሰፈሩ ሰብአዊ መብቶች እንዲሁም መሰረታዊ ነጻነቶች እንደተጠበቁና የአመጽ ድርጊቶችም እንዲወግዱ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይና ሴኪዩሪቲ ፖሊሲ ቃል አቀባይዋ ካትሪን ሬይ በኩል ባወጣው መገለጫ አሳስቧል።