ኮሎኔል አበበ ገረሱ አዲስ አበባ ገቡ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 4/2010)በምርጫ 1997 በሕዝብ ላይ የደረሰውን ግድያ በመቃወምና የሕዝብ ድምጽ መሰረቁን በማውገዝ ሰራዊታቸውን ይዘው ኤርትራ ከገቡት ከፍተኛ መኮንኖች አንዱ ኮሎኔል አበበ ገረሱ አዲስ አበባ ገቡ።

ስርአቱን አውግዘው በተመሳሳይ ከሃገር የወጡት የኦሕዴድ መስራች አቶ ዮናታን ዲቢሳም በተመሳሳይ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተሰምቷል።

ስርአቱን ተቃውመው ከሃገር የወጡትና በትግል ላይ የቆዩት ኮለኔል አበበ ገረሱና አቶ ዮናታን ዲቢሳ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በግብጽ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ነው።

በግብጽ ካይሮ የነበሩት ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በአንድ አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

የኦሕዴድ መስራች የነበሩት አቶ ዮናታን ዲቢሳ በኢትዮጵያ በሕወሃት የበላይነት በሀገሪቱ ውስጥ የማይፈጸመውን ግፍና ጭቆና በመቃወም በተለይም በኦሮሞ ላይ ይደርሳል ያሉትን ጥቃት በማውገዝ ስርአቱን ጥለው ከተሰደዱ ወደ 20 አመታት አስቆጥረዋል።

በምርጫ 1997 ማግስት ስርአቱን በማውገዝ ከፍተኛ የሰራዊት ሃይል በማስከተል ድንበር አቋርጠው ኤርትራ የገቡት ኮለኔል አበበ ገረሱ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ውስጥ ታቅፈው በትግል ውስጥ ቆይተዋል።

በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ውስጥ በተፈጠረው ክፍፍል አንዱን አንጃ በመያዝ መገንጠል የሚለውን የፕሮግራሙን ክፍል በመሰረዝ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

የእንቅስቃሴያቸው መዳከምን ተከትሎ ኮለኔል አበበ ገረሱና ጄኔራል ከማል ገልቹ ከኤርትራ ወደ ሌሎች የአካባቢው ሃገራት ተጉዘዋል።

ኮለኔል አበበ ገረሱ በአስመራ ቆይታቸው በኢሳት “የጸጥታ  ሃይሎች” ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ ተሳትፎም ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ጄኔራል ከማል ገልቹም በተመሳሳይ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ከነ ጄኔራል ከማል ገልቹ በኋላ በተመሳሳይ ስርአቱን ከድተው ወደ ኤርትራ የተጓዙት ብርጋዴር ጄኔራል ሃይሉ ጎንፋ በአሁኑ ወቅት በሲውዲን ስቶኮሆልም የሚገኙ ሲሆን ኮሎኔል ገመቹ አያና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ውስጥ በማሳተፍ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ስርአቱን አውግዘው በተመሳሳይ ከሃገር የወጡት የኦሕዴድ መስራች አቶ ዮናታን ዲቢሳም ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ታውቋል።

አቶ ዮናታን ሃገራቸውን ለቀው ከወጡ በኋላ በኦነግ ውስጥ የፖለቲካ ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ መቆየታቸውም ታውቋል።

ተቀማጭነታቸውን በኤርትራ አድርገው እንደነበር የተገለጸው አቶ ዮናታን ከሃገራቸው ከወጡም 17 አመታትን ማስቆጠራቸው ተመልክቷል።