ስር ነቀል ለውጥ የማያመጣ ከሆነ ጭብጨባው ወደ ጩኽት ሊቀየር ይችላል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 4/2010)የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጉዞ ስር ነቀል ለውጥ የማያመጣ ከሆነ ጭብጨባው ወደ ጩኽት ሊቀየር እንደሚችል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ገለጸ።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ለውጥ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ቢያንስ የሞራል ድጋፍ መስጠት እንደሚገባም አመልክቷል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ይህንን የተናገረው ለእሱና ለባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደ የምስጋና ስነ-ስርአት ላይ ነው።

ስድስት አመታት ከመንፈቅ በወህኒ ያሳለፈው ጋዜጠኛ እስክንድር በየካቲት መጀመሪያ ከወህኒ መፈታቱ ይታወሳል።

ከወር በፊት ዋሽንግተን ዲሲ የገባውና ደማቅ አቀባበል የጠበቀው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ትላንት በተካሄደው የምስጋና ስነስርአት በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ምስጋና አቅርቧል።

ምስጋናው የእሱ ብቻ ሳይሆን ከወህኒ የተፈቱ አጋሮቹ ጭምር መሆኑንም አመልክቷል።

በመከራ ወቅት መጽናኛና ተስፋ ሆናችሁናል ሲልም ማስጋናውን አቅርቧል።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባደረገው ሰፊ ንግግርም በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያለውን የሃይል አሰላለፍ በጥልቀት ተመልክቷል።

የጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል ሳሞራ የኑስና የደህንነት ዋና ሃላፊው የአቶ ጌታቸው አሰፋ መነሳት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጉልበት እየጨመሩ መምጣታቸውን ያሳያል ብሏል።

ይህንን ርምጃቸውን በፍጥነት ቀጥለው የለውጥ እንቅፋቶችን ካልጠረጉ እንደገና ተሰባስበው ሒደቱን ሊቀለብሱና እሳቸው ላይም ርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

እሳቸው ለምሳ ሲያስቧቸው እነርሱ ቁርስ እንዳያደርጓቸው በእጅጉ መጠንቀቅ እንዳለባቸው መክሯል።

በዚህ ሒደት ውስጥ ዶክተር አብይን ቢያንስ በሞራል መደገፍ ያስፈልጋል ብሏል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጉዞ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ይኖርበታል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ጭብጨባው ወደ ጩኽት ሊቀየር እንደሚችል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አሳስቧል።

በአንድ ፓርቲ፣ከአንድ ፓርቲ ውስጥም በሕወሃት የበላይነት ዙሪያ በተቃኘና ሕዝብ ባልመከረበት ሕገ መንግስት ዙሪያ መሰባሰብ አይቻልም ሲልም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ተናግሯል።

ሕዝብ የመከረበት ሕገመንግት የማጽደቅ ስራ አብይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም አሳስቧል።

በሰላማዊም ሆነ በመሳሪያ የሚታገሉ ዋና ዋና ሃይሎችን ያሳተፈ ሁሉን አቀፍ ጉባኤ እንዲጠራም ጥሪ አቅርቧል።

ከዚህ በመለስ በጥገና የሚመጣ ዘላቂ ሰላምም ሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንደማይኖር አመልክቷል።

ሒደቱ በጥገና የሚቆም ከሆነ ለዶክተር አብይ እየጎረፈ ያለው ጭብጨባ ወደ ጩኽት ሊቀየር እንደሚችልም አሳስቧል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ በጥገና እንዳይቆም ሕዝቡን በማስተባበር ለሚቀርቡ ጥያቄዎች በግንባር ቀደምትነት እንደሚሰለፍም ቃል ገብቷል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የታደመበትና አዳራሽ በመሙላቱ ብዙዎች ለመመለስ የተገደዱበት የዋሽንግተን ዲሲው የእስክንድር ነጋና የባለቤቱ የሰርካለም ፋሲል የምስጋና ፕሮግራም የተለያዩ ሽልማቶን በማበርከት በድምቀት ተጠናቋል።