ሚያዚያ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የስዊድን ጋዜጠኞችን ለማስፈታት የአውሮፓ ህብረት ወደ ኢትዮጵያ የላካቸው ሉዊስ ሚሸል፣ መለስ ዜናዊ ጋዜጠኞችን የማይፈታቸው በክብርት አና ጎሜዝ የተነሳ መሆኑን ለስራ ባልደረቦቻቸው መናገራቸውን ታማኝ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለኢሳት ገልጠዋል። መለስ ዜናዊ ጋዜጠኞችን ለመፍታት ይፈልጋል፣ ነገር ግን በውይይታችን ወቅት ደጋግሞ የሚያነሳው ስለ ወ/ሮ አና ጎሜዝ ነው፤ እንደተረዳሁት ለጋዜጠኞቹ መፈታት እንቅፋት የሆነችው አና ጎሜዝ ናት በማለት መናገራቸው ታውቋል።
የመለስ ወዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአውሮፓ ፓርላማ አባሉ ሉዊስ ሚቸል ፣ ከሁለት ወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ከመለስ ዜናዊ ጋር መነጋገራቸው እንዲሁም በቃሊቲ የሚገኙ ጋዜጠኞችን መጎብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከጉብኝታቸው በሁዋላም ጋዜጠኞቹ በሳምንታት ውስጥ በይቅርታ እንደሚፈቱ ገልጠዋል። ይሁን እንጅ የእርሳቸው መግለጫ በተሰጠ በማግስቱ አቶ በረከት ጋዜጠኞቹ እንደማይፈቱ ግልጽ ማድረጋቸው ይታወሳል። ሉዊስ ሚቸል ለጋዜጠኞች አለመፈታት ምክንያቱ መለስ ራሳቸው ናቸው ከማለት አና ጎሜዝ ናቸው ማለታቸው ብዙ ዲፐሎማቶችን ማስገረሙም ታውቛል። የስዊድን መንግስት በሉዊስ ሚቸል የዲፐሎማሲ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የሆነ አመኔታ ጥሎ እንደነበር ታውቋል።
___________________________________________________________________________________________________ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide