የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በአል በመላው አገሪቱ ተከበረ

ሚያዚያ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በመላው አገሪቱ የሚገኙ ክርስቲያኖች ያዛሬውን የስቅለት በአል ያሳለፉት በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት የስግደትና  የጸሎት ስነስርአት በማድረግ ነው። ዘጋቢያችን ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዳሉት ቀኑ እየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በሙሉ የከፈለውን እዳ በማስታወስ ምንጊዜም መልካም ማድረግ እንዳለብን የሚያስገነዘብ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከእለት ወደ እለት እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነት እና የብር የመግዛት አቅም መዳከም በዓልን ለማክበር ይቅርና የእለት ኑሯቸውን ለመግፋት እንደከበዳቸው ዘጋቢያችን ያናገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጸዋል፡፡ የፋሲካ በዓል ገበያም እጅግ የተቀዛቀዘ መሆኑን ተዟዙሮ ተመልክቷል፡፡

በመሐል ከተማ በሚገኙ የገበያ ሥፍራዎች የአንድ ዶሮ ዋጋ ከ130 እስከ 200 ብር በልማድ /እጅ ላይ ከበድ ባለ ልኬት/ የሚሸጥ ሲሆን (በአንፃራዊነት የሴት ዶሮ ዋጋ ቀነስ ብሎ ከ100 ብር እስከ 135 ብር ሲሸጥ ታይቷል) የኤልፎራ እና መሰል የዶሮ እርባታ ድርጅቶች ዶሮች ደግሞ በ90 ብር ገበያ ላይ ውለዋል፡፡ አንድ የዶሮ እንቁላል ደግሞ በ2 ብር ከ50 ሣንቲም በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡

ፒያሳ በሚገኘው አትክልት ተራ እና መርካቶ በሚገኘው አትክልት ተራ ውስጥ አንድ ኪሎ የአበሻ ሽንኩርት በ15 ብር ዋጋ እየተሸጠ ሲሆን አንድ ኪሎ የፈረንጅ ሽንኩርት ደግሞ ከ 10 እስከ 11 ብር ከ50 ሳንቲም በመሸጥ ላይ ይገኛል (በአንፃራዊነትም ከዶሮ እና በግ የገበያ ሥፍራዎች ይልቅ አትክልት ተራ የሽንኩርት ገበያ ሞቅ ብሎ ይታያል) ሲል ዘጋቢያችን በቦታው ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡

በመርካቶ ቂቤ በረንዳ አንድ ኪሎ ሸኖ ለጋ ቅቤ (እንደ አይነቱ) ከ180 እስከ 200 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ የበሰለው ቅቤ ደግሞ ከ150 እስከ 160 ብር ዋጋ /እንደ ብስል ደረጃው/ ሲሸጥ አንድ ኪሎ አይብ ከ55 እስከ 60 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

በአዲሱ ገበያ የበግ እና የቀንድ ከብት መሸጫ ሥፍራ አንድ ትንሽ በግ እስከ 700 ብር ሲሸጥ፣ መካከለኛ የተባሉ በጎች ደግሞ ከ1000 ብር በላይ ሲሆኑ ተለቅ፣ ገዘፍ ብለው የሚታዩ በጎች ደግሞ እስከ 2500 ብር ሲገበያዩ ዘጋቢያችን ተመልክቷል፡፡ በየአካባቢው ባሉ ሥፍራዎች የሚገኙ የበሬ ሥጋ ክፍፍልና ቅርጫ ደግሞ ሙሉ መደብ ከ800 ብር እስከ 1000 ብር ሲሆን ግማሽ መደብ ደግሞ ዝቅተኛው 400 ብር እና ከዚያ በላይ መሆኑን ዘጋቢያችን ተመልክቷል፡፡

ከመርካቶ ዶሮ ተራ አንዲት ሴት ዶሮ እና እንቁላል ገዝተው ሲመለሱ ዘጋቢያችን ያናገራቸው ወ/ሮ ፈትለወርቅ አባተ በባላቸው ጡረታና በጉሊት ንግድ ገቢ የስምንት ቤተሰብ አስተዳዳሪ /እማወራ/ መሆናቸውን ገልጸው ዘንድሮ ለፋሲከላ በዓል ሁለት ዶሮ እና ተጓዳኝ ሸቀጦችን ለመግዛት አስቤ ይዤ የወጣሁት ብር አንድ ዶሮ እና ስምንት እንቁላል ብቻ ገዝቼ ተመለስኩ፤ የአንዲት ዶሮን ብልት ምኑን ከምኑ አድርጌ ልጆቼን ፆም እንደማስፈታ መድሃኒያለም ክርስቶስ ነው የሚያውቀው፣ ቅርጫ እንኳ መግባት አልቻልኩም፣ ሁሉ ነገር ከአቅሜ በላይ ሆነ፤ መኖር አቅቶኛል ብለዋል፡፡

መርካቶ ቂቤ በረንዳ ሁለት መደብ ይዘው የሚነግዱት አቶ በላይ ቢራቱ ደግሞ ገበያው እንኳን የፋሲካ ሊመስል ይቅርና ከአዘቦት ቀኑም ቀንሷል ሰው በኑሮ ስለተዳከመ ቅቤን የድሎት ምግብ አድርጎት ትቶታል፣ ሰው ቅቤ አልገዛም ማለት ደግሞ ምናልባት ከእርድና ከሥጋም እርቋል ማለት ነው፣ ምናልባት ገበያው ዛሬን እና ነገን ይነቃቃ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን በማለት የግንዛቤያቸውን ተናግረዋል፡፡

___________________________________________________________________________________________________ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide