ሰሜን ሱዳን የደቡብ ሱዳንን ጦር ለመውጋት ጦሯን መላኩዋ ተሰማ

ሚያዚያ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ከሳምንታት በፊት በደቡብ እና በሰሜን ሱዳን መንግስታት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ተጥሶ ሁለቱ አገሮች ወደ ለየለት እና ደም አፋሳሽ ጦርነት እያመሩ መሆኑን የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አስታውቀዋል። ሁለቱም ድርጅቶች መንግስታቱ የጦርነት ነጋሪት መጎሸማቸውን ትተው ለሰላም እድል እንዲሰጡ ቢወተውቱም፣ መንግስታቱ ግን የሚቀበሉት አልሆነም።

ሰሜን ሱዳን የነዳጅ ጉድጓድ የሚገኝበትን የሄግሊግ ከተማን መልሳ ለመያዝ ጦሩዋን ወደ ስፍራው እያጓጓዘች መሆኑ ሲታወቅ፣ ደቡብ ሱዳን ደግሞ ከሰሜኑ ሊሰነዘርባት የሚችለውን ጥቃት በመፍራት ሀይሉዋን በአካባቢው እያጠናከረች ነው። ዛሬ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ደግሞ ሁለቱ ሀይሎች ከሄግሊግ 40 ኪሎሜትር በሚርቅ ቦታ ላይ ጦርነት ጀምረዋል።

የሁለቱ አገሮች ወደ ሙሉ  ጦርነት መግባት የአካባቢውን ሰላም ያደፈርሰዋል የሚል ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል። ሁለቱም አገሮች ከገጠማቸው የኢኮኖሚ ቀውስ አንጻር ከታየ፣ የአሁኑ ጦርነት ሱዳንን ወደ ሶማሊያ የሚቀይር ይሆናል በማለት ተንታኞች ይናገራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የደቡብ ሱዳን መንግስት በህገ ወጥ መንገድ  ገብተዋል ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በመሰር ላይ ነው። በቅርቡ በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት መካከል በጋምቤላ በተካሄደው ውይይት ደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ እየተሻገሩ ጥቃት በሚፈጽሙ የኢትዮጵያ ተወላጆች ላይ ቁጥጥር እንድታደርግ ፣ የኢትዮጵያን የልኡካን ቡድን የመሩት አለቃ ጸጋየ መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።  ምንም እንኳ ደቡብ ሱዳን ወደ አገሩዋ በሚገቡ የጋምቤላ ተወላጆች ላይ ቁጥጥር እንደማታደርግ አስታውቃ የነበረ ቢሆንም፣ ከደቡብ ሱዳን የደረሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን በርካታ ኢትዮጵያውያን እየተያዙ በመታሰር ላይ ናቸው።

_______________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide