መንግስት በአማራ ተወላጆች ላይ የወሰደውን እርምጃ ኦነግ አወገዘ

ሚያዚያ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ባወጣው ጠንካራ መግለጫ የህወሀት አገዛዝ የአማራ ተወላጆች ከደቡብ ክልል እንዲወጡ ማድረጉ ፣ አገዛዙ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት የስልጣን እድሜውን ለማራዘም የሚጠቀምበት ስልት በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል ብሎአል።  የህወሀት አገዛዝ የአፋር፣ ጋምቤላ ፣ ደቡብና የ ኦሮሞ ተወላጆችን ከማፈናቀል አልፎ ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ በማጋጨት የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ይሞክራል የሚለው ኦነግ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በመሆን ይህን ሰይጣናዊ ስራ ማጋለጥ ብቻ ሳይሆን ይህን የሚያቅዱትን  እና የሚያስፈጽሙትን በጋር ታግሎ ሊያስወግዳቸው ይገባል ብሎአል።

በጄኔራል ከማል ገልቹ ስም የወጣው መግለጫ የህወሀት አገዛዝ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጽመው ዘግናኝ ድርጊት በሰውልጆች ላይ በተፈጸመ ወንጀል እንደሚያስጠይቀው ገልጧል። ኦነግ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ውስጥ በመረጡበት ቦታ የመኖር መብት እንዳላቸውም አስምሮበታል። 

በሌላ ዜና ደግሞ 4ኛዉ የኦሮሞ የግንዛቤ ቀን ተከብሮአል።

ሚያዝያ 1 ቀን 2004 በሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ በታሰበዉ 4ኛዉ የኦሮሞ የግንዛቤ ቀን ስብሰባ ላይ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች  ተወካይ ባሰሙት ንግግር እኤአ ከ1991 ጀምሮ ክልሉን በወታደራዊ አገዛዝ የተቆጣጠረዉ የህወሃት መንግሰት የፈፀመዉን የሰብኣዊ መብት ረገጣዎች በዝርዝር አስረድተዋል።

የራስን እድል በራስ የመወሰንን መብት ጨምሮ የስራ ፤ የትምህርት እና ባህሉን የማስከበር መብቶቹን እንደተነፈገ በመግለፅ የኦሮምኛ ቋንቋ ስሞችን የስራ እድል ለማግኘት ሲባል መደበቅና መለወጥ እንደተገደደ እንዲሁም ባህልና ታሪኩን ለማሳደግ ጥረት ያደረጉ የሜጫ ቱለማ ማህበር መሪዎችና ደጋፊዎች በእስር በመማቀቅ ላይ መገኘታቸዉ ተብራርቷል።

ከዚህ በተጨማሪ በህወሃት መንግሰትና በዉጭ አገር መንግስታት በመካሄድ ላይ ስላለዉ የመሬት ቅርምት ገለፃ መደረጉን ገዳ ድረ ገፅ አመልክቷል።

_______________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide