ግንቦት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ወግ አጥባቂው የካናዳ መንግስት ለውጪ እርዳታ ከሚሰጠው ገንዘብ ውስጥ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት 377 ሚሊዮን ዶላር ለመቀነስ መወሰኑን “ኦታዋ ሲቲዝን”ዘገበ።
የካናዳ ዓለማቀፍ የልማት ፕሮግራም -ሲ.አይ.ዲ.ኤ፤ የሁለትዮሽ ፕሮግራሙን ከሚቀንስባቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ሆና መለየቷን የካናዳ ዓለማቀፍ ትብብር ሚኒስትር ቤቭ ኦዳ ገልጸዋል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ከምታገኘው እርዳታ ምን ያህል መጠን እንደሚቀነስባት የትብብር ሚኒስቴር ጽህፈት ቤቱ አልገለጸም።
እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ 2010-11 የበጀት ዓመት ኢትዮጵያ-ከካናዳ 176 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፤ ከሀይቲ እና ከ አፍጋኒስታን ቀጥሎ ኢትዮጵያ በሦስተኛ ደረጃ የካናዳን እርዳታ ስታገኝ የቆየች አገር መሆኗን ጠቁመዋል።
በዚህ ዓመት የሚደረገው የእርዳታ ቅነሳ ባለፈው ዓመት በተከሰተውና እስካሁን በቀጠለው ከፍተኛ ድርቅ ምክንያት ከአስር ሰው አንድኛው ሲያገኙት የቆዩትን የምግብ እህል እርዳታ እንዲቋረጥ በማድረግ፤ አገሪቱን ለምግብ እህል እጥረት ሊያጋልጣት እንደሚችል ኦታዋ ሲትዝን ሥጋቱን ገልጻል።
የ እርዳታ ቅነሳው ፕሮግራም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች 12 ያህል የዓለማችን ደሀ አገሮችን የሚያጠቃልል ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል ቤኒን፣ኒጀር፣ካምቦዲያ፣ ቻይና፣ኔፓል፣ሩዋንዳ፣ዛምቢያ እና ዚምባቡዌ ይገኙበታል።
ይህ ዜና ይፋ የሆነውም፤ ባለፈው አርብ በአዲስ አበባ በተከፈተው እና የካናዳ ዓለማቀፍ የትብብር ሚኒስቴር ቤቭ ኦዳ በተሳተፉበት የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ወቅት የአቶ መለስ ዜናዊ ጭፍን አድናቂ ተደርጎ ይቆጠር የነበረው አይሪሻዊው የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃን ቦብ ጊልዶፍ ፣ የመለስ መንግስት አሁን ለሚታየው የህዝብ ቁጣ መልስ መስጠት ካልቻለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታየው የማህበራዊ ለውጥ ሊፈራርስ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
የቢቢሲው ማርቲን ፕላውት ከአመት በፊት በ1970ዎቹ ለትግራይ ህዝብ የተሰጠውን የእህል እርዳታ፣ አብዛኛውን መጠን ህወሀት ለጦር መሳሪያ መግዣ እንዳዋለው ማጋለጡን ተከትሎ ፣ የህወሀት ጠበቃ በመሆን በግንባር ቀደምነት የተሰለፈው ሰር ቦብ ጊልዶፍ እንደነበር ይታወቃል። ለኢትዮጵያ እርዳታ በማሰባሰብ በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው ቦብ ጊልዶፍ፣ የቀድሞው የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር የነበሩት ቶኒ ብለየር ባቋቋሙት የአፍሪካ ኮሚሽን ድርጅት ውስጥም ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር በጋራ ሰርቷል። በቦብ ጊልዶፍና በአቶ መለስ መካከል የነበረው ጥብቅ ግንኙነት መሻከር የጀመረው በምርጫ 97 ወቅት ቢሆንም፣ ከቢቢሲ ዘገባ ጋር በተያያዘ በሁለቱ ግለሰቦች መካከል የነበረው ግንኙነት እንደገና ለመታደስ ችሎ ነበር። ሰር ቦብ ጊልዶፍ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአለማቀፍ የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ ካቀና በሁዋላ ከኤኤፍ ፒ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ፣ የመለስን መንግስት ክፉኛ ሊያስቆጣ የሚችል ንግግር ተናግሯል።
ሰር ቦብ ጊልዶፍ አቶ መለስ ዜናዊ ታጋሽና ሰዎች በአገራቸው ጉዳዮች እንዲሳተፉ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን እንዳለባቸው ጠቁሞ ፣ አሁን እንደሚያዳርጉት ዜጎችን ምንም አይነት ጠንካራ ትችት መጻፍ አትችሉም እያሉ የሚከለክሉትን የአፈና ስርአት የሚቀጥሉበት ከሆነ፣አገዛዙ ችግር ውስጥ መሆኑን ያሳያል ብሎአል። ገልዶፍ እንዳለው ህዝቡ በአገሩ ጉዳይ እንዲሳተፍ እና አሁን የሚታየው የተወጠረ አየር እንዲተነፍስ ፣ መንግስት ክዳኑን በመክፈት ማስተንፈስ አለበት ። የምእራቡ አለም ያደገው ሀሳብን በነጻነት መግለጽ በመቻሉ ነው ያለው ቦብ ጊልዶፍ፣ ኢትዮጵያም የምእራቡን አለም ምሳሌ መከተል እንደሚገባት መክሯል። ኢትዮጵያ፣ ታጋሽ ካልሆነች፣ በቅርቡ የተገኘው የኢኮኖሚና የምህበራዊ ለውጥ ሙሉ በሙሉ ሊቀለበስ ይችላል ሲል አስጠንቅቋል
ህዝቡን ማሳተፍ ካልቻሉ ሁሉም ነገር ይቆማል ያለው የሙዚቃ ባለሙያው፣ መለስ የመንግስትን ምንነት መረዳት የሚችል አዋቂ ሰው ነው ሲልም ተናግሯል።
የእርዳታ አቀንቃኙና የሙዚቃ ኮከቡ ጊልዶፍ በኢትዮጵያ ያለው የፌደራሊዝም ስርአት በመላ አገሪቱ አመጽ እና ቅሬታ እየፈጠረ መሆኑንም አልሸሸገም። “በተለይ ተቃዋሚዎች በአገራቸው ፖለቲካ ድምጻቸው እንዲሰማ የሚያደርግ መድረክ ካልተሰጣቸው ብሄራዊ አደጋ ይፋጥራሉ” ሲል ያስጠነቀቀው ጊልዶፍ፣ የህዝብን ድምጽ ልታፍን አትችልም ካለ በሁዋላ፣ “በአገሪቱ ውስጥ ሁሉንም የሚያሳትፍ ስርአት ከተዘረጋ፣ ህዝቡ ተቃውሞን ማሰማት ከቻለ፣ ሲቪል ሶሳይቲው እንዲተነፍስ ከተፈቀደለት፣ አሁን ለነጻነት የሚደረጉ ትግሎች ሁሉ እየቀነሱ ሲመጡ ልናይ እንችላለን፣ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ሲቪል ሶሳይቲው በመጨረሻ ያሸንፋል። ብዙ ስለሆኑ ያሸንፋሉ፣ ህዝቡም መተንፈስ ይጀምራል።” ብሎአል።
የቦብ ጊልዶፍ ያልተጠበቀ አስተያየት የአለማቀፉ ማህበረሰብ በመለስ መንግስት ላይ ያለውን አመለካከት እንደገና እንዲመረምር ሊያደርገው ይችላል። በእንግሊዝ መንግስት ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው ጊልዶፍ፣ የመለስን መንግስት በጭፍን ከማምለክ ነጻ ወጥቶ፣ ነገሮችን በትኩረት ለማየት መቻሉ በዲፕሎማሲው ረገድ ለሲቪል ሶሳይቲውና ለተቃዋሚው ድል ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች። በቦብ ጊልዶፍ ደረጃ የሚገኝ የእርዳታ አቀንቃኝ፣ የኢትዮጵያ ማህበራዊ እድገት ሊቀለበስ ይችላል በሚል የሰጠው አስተያየት ምናልባትም በቅርቡ በአረብ አገራት የታየው አብዮት ያደረሰውን ጉዳት ከተመለከተ በሁዋላ የተገነዘበው ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች ያክላሉ። የጋዳፊ ሊቢያ በማህበራዊ እድገት ከፍተኛ ለውጥ የነበራት አገር ብትሆንም፣ አምባገነኑን ስርአት ለማስወገድ በተደረገው ትግል አገሪቷ ሙሉ በሙሉ መውደሟ ይታወሳል። በሶሪያ፣ በግብጽ እና በየመንም ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። የሰር ቦብ ጊልዶፍ የማንቂያ ደወል በአቶ መለስ ሊወደድ እንደማይችል ተንታኞች ይናገራሉ።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide