ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ቀዳሚ ትሆናለች ተባለ

ግንቦት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሪፖርተር አይኤም ኤፍን ጠቅሶ እንደዘገበው ኤርትራ በማእድን፣ በመሰረተ ልማት እና በእርሻው መስክ ባስመዘገበችው ውጤት ከምስራቅ አፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ቀዳሚ አገር ትሆናለች። ኤርትራ በ7.5 በመቶ እንደምታድግ የተነበው አይ ኤም ኤፍ፣ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 5 በመቶ ብቻ ያድጋል ብሎአል።

የመለስ መንግስት 11 በመቶ የኢኮኖሚ እደገት ማግኘቱን በተደጋጋሚ ሲገልጽ፣ የኤርትራ መንግስት በአንጻሩ ስለ አገሪቱ እድገት ምንም አይነት የፕሮፓጋንዳ ስራ ሲሰራ አይታይም። መገናኛ ብዙሀን ኤርትራ በኢኮኖሚው የደቀቀች፣ ልትፈራርስ የቀረበች አገር አድርገው በተደጋጋሚ ይዘግባሉ።  የአይኤም ኤፍ ሪፖርት እንደሚያሳየው ግን ኤርትራ ድምጿን አጥፍታ ከኢትዮጵያ የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኑዋን የሚያሳይ ነው።  ባለፈው አመት ከፍተኛ እድገት እንዳመጡ የሚወራላቸው ኢትዮጵያ እና ኬንያ በረሀብ መጠቃታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እርዳታ ከአለማቀፍ ለጋሾች ሲቀርብላቸው ኤርትራ ምንም የውጭ እርዳታ ሳታገኝ አመቱን አገባዳለች። አለማቀፉ ማህበረሰብ በበኩሉ ኤርትራ የረሀብተኛውን ቁጥር ሆን ብላ ትደብቃለች በማለት ሲከስ ይሰማል። ይሁን እንጅ የኤርትራ የኢኮኖሚ እድገት ዜና በተለይም የግብርናው ምርት ያለ ውጭ እርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳደገ በአለማቀፍ ተቋማት መመስከሩ፣ ለመለስ መንግስት እና በኤርትራ መንግስት ላይ ማእቀብ እንዲጣል ሲወተውቱ ለነበሩ የምእራብ መንግስታት የፕሮፓጋንዳ ስራ ትልቅ ጋሬጣ እንደሚፈጥርበት አንድ የተቃዋሚ አባል ተናግረዋል። የኤርትራ መንግስት በራስ መተማመን በሚል ፖሊሲው የውጭ እርዳታ አይቀበልም። በአንጻሩ የመለስ መንግስት በእየአመቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በእርዳታ መልክ ያገኛል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide