ታህሳስ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-10ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቁ ወደ ዩኒቨርስቲ መግባት ያልቻሉ ታዳጊ ወጣቶች መሰረተ ልማት ባልተሟላበት ፤ የኮምፒዩተር አቅርቦት በሌለበት ፤ የተሰናዳ የትምህርት ክፍል፣ ወንበር እና የማሰተማሪያ መርጃ መሳሪያዎች ሳይሟሉ እና ከተግባር መሳሪያዎች ጋር በደንብ ሳይተዋወቁ ተምረው ለምረቃ ይበቃሉ፡፡
በየአመቱ ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች የሚመክኑበት ይህ የትምህርት ዘርፍ አላማው ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ቢሆንም ውጤታማ ሊሆን አለመቻሉን ጥናቶች ያሳያሉ።
ተማሪዎች “በቂ እውቀት እና ትምህርት ማግኙት አልቻልንም ” በማለት አቤቱታ ቢያቀርቡም ከመንግስት ተገቢ መልስ አለማግኘታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ስዓት ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው በስራ ፈጠራ ወይም በስራ መስክ የተሰማሩት 10 በመቶ እንኳን መሙላት እንደማይችሉ ጥናቶችን ያሳያሉ።
መንግስት በገጠመው የበጀት እጥረት ለቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ከሚጠይቁት በጀት ግማሽ ያህሉን እንኳን ማሟላት ባለመቻሉ አንዳንድ ኮሌጆች የግቢያቸውን ሳር በመሸጥ እና በብድር ለመምህራን ደሞዝ ለመክፈል ተገደዋል፡፡
በአሁኑ ስዓት በሃገሪቱ ካሉ 173 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና ተቋማት ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚችሉት አስራ ሶስት ብቻ ናቸው፡፡ 119 ትምህርት ቤቶች ገና በጅምር ያሉ ሲሆን መንግስት ግንባታቸው በህዝብ መጠናቀቅ አለበት የሚል አቋም ይዟል።
በ2005 ዓ.ም በደረጃ አንድ ፣ በደረጃ ሁለት እና ሶስት በሰርተፍኬት ተመርቀው ለሙያ ብቃት ምዘና ፈተና ከወሰዱ 126 ሺ 642 ተማሪዎች ፈተናውን ማለፍ የቻሉት 26 በመቶዎች ብቻ ናቸው፡፡
“መንግስት ባላሰተማረን ትምህርት ፣ በአይናችን ያላየነውን መሳሪያ ለመፈተኛ በማቅረብ ያልሰጠንን ሊቀበለን በመፈለግ በአግባቡ መምራት ባልቻለው ሴክተር ውድቀታችንን አርድቶናል” ሲሉ ተማሪዎች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
አስረኛ ክፍል አጠናቀው በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት የተመረቁ ተማሪዎች በመንግስት ዩኒቨርስቲ የዲፕሎማ መርሃ ግብር መማር የሚችሉት የብቃት ፈተና ማለፍ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡