ከ20 ቀናት በፊት በድንገት ከኃላፊነታቸው የተነሱት የማዕድን ሚኒስትር ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉ በምክትላቸው አቶ ቶሎሳ ሻጊ ተተኩ፡፡

ታህሳስ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርላማው በጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ፊርማ የቀረበለትን ዕጩ ሚኒስትር አቶ ቶሎሳ ሻጊ ሞቲን ሹመት ተቀብሎ አጽድቆአል፡፡ አቶ ቶሎሳ የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን በማገልገል ላይ የነበሩ ሲሆን ከማዕድን ጋር ተያያዥ በሆኑ ስራዎች ከ20 ኣመታት በላይ አገልግለዋል፡፡

ከ16 ዓመታት በላይ በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውስጥ ከኤክስፐርትነት እስከ ሚኒስትር ዴኤታ ባሉት የኃላፊነት ቦታዎች ሲሰሩ የቆዩትና በጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተለያየ አደረጃጀት ይዞ ለሁለት ሲከፈል የማዕድን ሚኒስትር በመሆን በአቶ መለስ ዜናዊ አቅራቢነት የተሾሙት የኦህዴድ አባሏ ወ/ሮ ስንቅነሽ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ሳይነገር ከአማራው ክልል ፕሬዚደንት አቶ አያሌው ጎበዜ ጋር ባለሙሉ አምባሳደር በመሆን በፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ መሾማቸው ይታወሳል፡፡

ፓርላማው የአዲሱን ሰው ሹመት በተቀበለበት ስነስርኣት ቀደም ሲል ፓርላማው የሾማቸው ሰው በምን ምክንያት እንደተነሱ ሳይጠይቅ አዲስ ሰው መሾሙን የደረሰን ዜና ያስረዳል፡፡