ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በእስር ላይ የሚገኙት የድምጻችን ይሰማ የኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ካሚል ሸምሱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትንና የኢትዮጵያ ኡላማዎችን ምክር ቤትን በደንቡ ያልተሾሙና መርጫ ለማስተባባር ስልጣን የሌላቸው ናቸው በማለት ምክር ቤቱ እንዲታገድና እንዲበተንና ምርጫ እንዳይደረግ ይወሰንልን በማለት መክሰሳቸው ይታወሳል። ዳኛ አምባቸው ታረቀኝ መስከረም 23 ቀን 2005 ዓም በሰጡት ትእዛዝ ፍርድ ቤቱ በሀይማኖት ጉዳይ የመዳኘት ስልጣን ስለሌላው ጥያቄው አለመቀበሉን ፣ የእግድ ይሰጥልን ጥያቄውንም ያልተቀበለው መሆኑን በመግለጽ መዝገቡ መዘጋቱን ገልጿል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መስከረም 27 የተደረገውን የመጅሊስ ምርጫ አለመሳተፋቸውንና አለመደገፋቸውን መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ላለፈው አንድ አመት የተካሄደው የሙስሊሞች ተቃውሞ የመጅሊስ ምርጫ ከተካሄደ በሁዋላ አልተካሄደም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ሙስሊሙ ህገመንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ በነጻነት የእምነቱ መሪዎችን መምረጡን ሰሞኑን በፓርላማ ባደረጉት ንግግር መግለጻቸው ይታወሳል። በዚህ ንግግራቸው ሙስሊሙ ህገመንግስቱን የማያከብር ከሆነ እና በተቃውሞው የሚቀጥል ከሆነ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።
በማህበራዊ ድረገጾች ላይ የሚወጡ ጽሁፎች እንደሚያመለክቱት ግን ሙስሊሙ ተቃውሞውን ከነገ ጀምሮ ይቀጥላል። መንግስት ተቃውሞው እንዲቀጥል ይፍቀድ አይፍቀድ የታወቀ ነገር የለም። ምናልባትም መንግስት እንደሚለው እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ከሆነ ለአንድ አመት የተካሄደው ሰላማዊ ትግል ወደ ደም መፋሰስ ሊያመራ ይችላል።
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄደው ተቃውሞ ለመንግስት ቢጫ ካርድ ማሳየቱን፣ ቀዩ ካርድም ሊከተል እንደሚችል መግለጹ ይታወሳል።