በመንግስት አና በ ኦብነግ መካከል የተጀመረው ድርድር ሳይሳካ ቀረ

ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ለድርድሩ መደናቀፍ አንድኛቸው ሌለኛቸውን ተጠያቂ እያደረጉ ነው።

በኢትዮጵያ መንግስትና በኦጋዴ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር መካከል የተጀመረው ድርድር አለመሳካቱን የኢትዮጵያ መንግስት ገለጸ።

ናይሮቢ ሚገኘው የ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ ድርድሩ የከሸፈው ኦብነግ የ ኢትዮጵያን ህገ-መንግስት ባለመቀበሉ ነው ሲል፤ኦብነግ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ አላስፈላጊ ቅደመ-ሁኔታዎችን በማስቀመጥ በድርድሩ ላይ እንቅፋት የፈጠረው የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን ገልጿል።

በጀነራል መሀመድ ኡስማን ከሚመራው የ ኦብነግ አንድ ክፍል ጋር እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ ኦክቶበር 15 እስከ 17-2012 ድረስ በናይሮቢ ድርድር ሲደረግ መቆየቱን የገለፀው የኢትዮጵያ መንግስት፤ይሁንና ኦብነግ ህገ-መንግስቱን ባለመቀበሉና በህገ-መንግስታዊው ማዕቀፍ ስር ሆኖ ለመስራት ባለመፈለጉ ድርድሩ ተቋርጧል ብሏል።

ከ ኦብነግ አመራሮች ጋር ድርድር ሲያደርግ የነበረው በመከላከያ ሚኒስትሩ በ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ የተመራ የልዑካን ቡድን እንደነበር በመግለጫው ተጠቁሟል።

ከ ኢትዮጵያ መንግስት ጋር ድርድር የጀመረው ኦብነግ ባወጣው መግለጫ  ግን ፤አላስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታ በማስቀመጥ የሰላም ድርድሩ ላይ እንቅፋት የፈጠረው ያለው የ ኢትዮጵያ መንግሰት ነው ብሏል።

የኦብነግ ልዑካን ቡድን መሪ የሆኑት የድርጅቱ የውጪ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አብዲራሂም ማህዲ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት  ባቀረበው  የ እንደራደር ጥያቄ መሰረት በኬንያ አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር የተደናቀፈው በራሱ በኢትዮጵያ መንግስት ነው።

በመጀመሪያው ዙር መደበኛ ውይይት በ አጠቃላይ የውይይቱ መርህ፣ ሞዳሊቲና አጀንዳዎች ዙሪያ የነበረው ንግግር በጥሩ ሁኔታ ቀጥሎ እንደነበር ያወሳው ኦብነግ፤ በሁለተኛው ዙር ውይይት ላይ ግን የ ኢትዮጵያ መንግስት የተስማማባቸውን ነጥቦች ሊያከብር አልቻለም ብሏል።

በድርድር መርህ መሰረት በ እኩልነትና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ድርድር መደረግ ቢኖርበትም የ ኢትዮጵያ መንግስት ግን ከዚህ መርህ ውጪ አላስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጡ ድርድሩ መደናቀፉን ከግንባሩ መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።

የኦብነግ የውጭ  ግንኙነት ሃለፊ የሆኑት አቶ ሀሰን አብዱላሂ ከኢሳት ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል