ሚያዚያ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ከከማሺ ዞን ተፈናቅለው በፍኖሰላም ከተማ ሰፍረው የቆዩት የአማራ ተወላጆች ያሶ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ አንድ ጫካ ውስጥ እንዲሰፍሩ ከተደረጉ በሁዋላ ዛሬ አርብ ከሰአት በሁዋላ ወደ የቀበሌያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ኢሳት ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ገልጸዋል።
ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ አብዛኛው ተፈናቃይ ወደ የቀበሌው የተጓዘ ሲሆን ቀሪዎቹም ወደ ቦታቸው ለመመለስ መኪና በመጠባበቅ ላይ ናቸው።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ተፈናቃይ ወደ ቀበሌያቸው መመለሳቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው ቢናገሩም፣ የቀበሌ ሹሞች አንረከብም በማለታቸው ወደ ቤታቸው ለመግባት እንዳልቻሉ ገልጸዋል። የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ” መሬታችሁን ሊነጥቁዋችሁ ነው” በማለት የእዞሩ መቀስቀሳቸው ተፈናቃዮቹ የደህንነት ስጋት እንደገባቸውም አልሸሸጉም። የአማራ ክልል ፖሊሶች ያሳዩትን ትብብርም ተፈናቃዩ አድንቀዋል። የአማራ ክልል ፖሊሶች ቀበሌዎች ድረስ በመውረድ የቀበሌ ሊቀመናብርት ተፈናቃዮችን እንዲቀበሉ ለማግባባት እየሞከሩ ነው።
በጉዳዩ ዙሪያ ላይ የዞኑንም ሆነ የወረዳውን ሹሞች አግኝቶ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ከመተከል ዞን ተፈናቅለው በቻግኒ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አለመመለሳቸውን ትናንት መዘገባችን ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በስዊድን የሚኖሩ ኢትዮጵያን በአማራ ተወላጆች ላይ የደረሰውን መፈናቀል በማውገዝ በአገሪቱ ፓርላማ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ለስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ለአፍሪካ ቢሮ ባለስልጣናት አቅርበዋል። የስዊድን መንግስት ማንኛውንም ሰነዶች ኢትዮጵያውያን ቢያቀርቡ የስዊዲን መንግስት ጉዳዩን በትኩርት እንደሚከታተለው ቃል መግባቱ ታውቋል።
በሰልፉ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን መንግስት በአማራ ተወላጆች ላይ የፈጸመው ድርጊት እንዳስቆጣቸው ለኢሳት ገልጸዋል።