ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ፍትህ ይሰጠን በማለት ተቃውሞ ሲያሰሙ ዋሉ

ሚያዚያ ፬  (አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የአርብ ስግደትን በማስከተል ከአንድ አመት በላይ ሲካሄድ የነበረው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን የመብታችን ይከበር ጥያቄ፣ በዚህ ሳምንት ” ፍትህ ፍትህ” በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል።

በአዲስ አበባ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች “ፍትህ ” የሚል ጽሁፍ የያዙ ወረቀቶችን በመያዝ ፍትህን ሲጠይቁ የዋሉ ሲሆን፣ ፍትህ አጥተው በእስር ቤት የሚሰቃዩ  መሪዎቻቸውን እጃቸውን በማጣመር በድጋሜ አስበዋቸዋል። የፌደራል ፖሊስ አባላት በብዛት በታዩበት በዛሬው ተቃውሞ ፣ ምንም አይነት ግጭት አለመፈጠሩን ለማወቅ ተችሎአል።

በአዳማ ፍትህ የጠየቁ ሙስሊሞች በፖሊሶች ተደብድበው እንዲባረሩ ተደርጓል። በእስር ላይ በሚገኙት ሙስሊም መሪዎች ላይ ምንም አይነት ጠንካራ የሰነድም ሆነ የሰዎች ማስረጃ አለመቅረባቸውን የውስጥ ምንጮች ይናገራሉ። አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም እንዲሁ የመሪዎቹ የፍርድ ቤት ሂደት ነጻና ፍትሀዊ አይደለም በማለት አጠቃላይ ሂደቱን እያጣጣሉት ነው።