ኢህአዴግ “ሕዝቡ ለመምረጥ ላይወጣ ይችላል” በሚል ስጋት ውስጥ ገብቷል

ሚያዚያ ፬  (አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ኢህአዴግ በመጪው እሁድ ብቻውን በሚወዳደርበት የአዲስአበባ እና የአካባቢ ምርጫ ላይ ለመምረጥ የተመዘገበው ሕዝብ ወጥቶ ላይመርጥ ይችላል በሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቁን ምንጮቻንን ጠቆሙ፡፡

ከምርጫ በፊት ባሉት ችግሮች ላይ ውይይት እንዲቀድም በይፋ ያቀረቡት ጥያቄ በኢህአዴግና በኢህአዴግ መራሹ ምርጫ ቦርድ በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱን ተከትሎ ከ28 በላይ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን፣ የኢህአዴግ አጋር እንደሆነ የሚነገርለት ኢዴፓ የተባለው ፓርቲም ከምርጫው ሙሉ በሙሉ ላለመውጣት በአንድ ዕጩ ብቻ ለውድድር መቅረቡ ምርጫው በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ጎድቶታል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከታህሳስ 22 እስከ ጥር 21/2005 የተካሄደው የመራጮች መደበኛ ምዝገባ ተቀዛቅዞ የከረመ ሲሆን ኢህአዴግ የሚቆጣጠረው ቦርዱ ግን ካለፉት ጊዜያት የበለጠ መራጭ መመዝገቡን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ደጋግሞ ሲናገር መክረሙ የሚታወስ ነው፡፡
ለአዲስአበባ እና ለአካባቢ ምርጫ የሚያስፈልጉ ዕጩዎች ከአራት ሚሊየን ተኩል በላይ ሲሆኑ ኢህአዴግ በየዓመቱ ከምርጫ ቦርድ ከሚሰጠው ከሰባት ሚሊየን ብር በላይ የሚቆጠር የገንዘብ ድጎማ ላይ እየቆነጠረ ተቆራጭ የሚያደርግላቸው ጥቂት ፓርቲዎች በጠቅላላ ያቀረቡት ዕጩዎች ቁጥር ብዛት ከ500 የማይበልጥ በመሆኑ የእነሱም የይስሙላ ተሳትፎ ግንባሩን ብቻውን ከመወዳደር እንዳላዳነው ታውቋል፡፡

ከነዚህ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በትክክል ለመምረጥ ተመዝግበዋል የተባሉ ዜጎች የምርጫው ዕለት ከመራጭነት እንዳያፈገፍጉ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ባሻገር ሰሞኑን በአዲስአበባ ከተማ መንገዶች ላይ በመኪና በመዘዋወር ሕዝቡ ኢህአዴግን እንዲመርጥ የሚያደርገው ቅስቀሳ አይሉት ማሰፈራሪያ በነዋሪው ዘንድ ትዝብት ላይ እየጣለው ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት እሁድም ስለምርጫው ገለጻ ለማድረግ በሚል ሰበብ ሕዝቡ በየቀበሌው ተገኝቶ ማብራሪያ የተሰጠው ሲሆን እግረመንገዱንም ሕዝቡ የተጀመረውን ልማት የሚያስቀጥልለትን ፓርቲ በጥንቃቄ እንዲመርጥ ምክር መለገሱን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ትናንት እና ዛሬ ደግሞ ኢህአዴግ ለእናቶች የንብ አርማ ያለበት የጆሮ ጌጥ አሰርቶ ቅስቀሳ ሲያደርግ ውሎአል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በየቀበሌው ቡና ተፈልቶ እናቶች ከቡናው ጋር ስለ ኢህአዴግ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል።

በኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት ለመምረጥ ከተመዘገበው ሕዝብ ውስጥ 99 በመቶ ያህሉም ባይመርጥ ገዥው ፓርቲ አሸናፊነቱን ከማወጅ የሚያግደው እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።  ለታይታና ለሚዲያ ፍጆታ ያህልም ቢሆን ሕዝቡ ላይወጣ ይችላል የሚል ስጋት የግንባሩን ከፍተኛ ካድሬዎች ጭምር እያስጨነቀ መሆኑ ታውቋል።

 

ከዚህ ቀደም በተለያዩ መድረኮች ላይ ህዝቡ በኑሮ ውድነት መማረሩ ፣ ከግንባታ ጋር ተያይዞ መፈናቀሎች መብዛታቸው፣የሙስሊሙ ህብረተሰብ ኩርፊያና የመሳሰሉት ለኢህአዴግ አደጋ መሆናቸው መገምገሙ የሚታወስ ነው፡፡የአዲስአበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ም/ቤቶች፣የወረዳና የቀበሌ ም/ቤቶች ምርጫ ሚያዚያ 6 ቀን 2005 የሚከናወን ሲሆን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል የቀበሌና የወረዳ ምርጫ ሚያዝያ 13 ቀን 2005 ዓ.ም ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡