የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ዳግም ቃጠሎ

መጋቢት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም  ኢሳት ዜና :-በማተሚያ ቤቱ የወረቀት ክምችት መጋዘን ላይ መጋቢት 13 ቀን 2006 ዓ.ም ከሰዓት በሃላ በተነሳ ድንገተኛ የእሳት አደጋ መጋዘኑን የጎዳ ሲሆን ትናንት ጠዋት ደግሞ በዚሁ መጋዘን ላይ ተመሳሳይ አደጋ አጋጥሞአል፡፡

የመጀመሪያው አደጋ በማተሚያ ቤቱ የወረቀት ክምችት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም ተመሳሳይ አደጋ በተመሳሳይ ቦታ ላይ በማጋጠሙ ፣በማተሚያ ቤቱ የማሽን እርጅናና ሌሎች አስተዳደራዊ ችግሮች በሕትመት ቀናቸው መውጣት ከነበረባቸው የግል ጋዜጦች መካከል ሪፖርተር እና ሰንደቅ የተባሉት በትናንትናው ቀን ታትመው ሊወጡ አልቻሉም፡፡
ለትናንቱ ቃጠሎው የተሰጠው ምክንያት ካለፈው ቃጠሎ የተዳፈነ እሳት ተቆስቁሶ ነው የሚል ሲሆን የመጀመሪያው ቃጠሎ በእሳት አደጋ ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ውሎ ከሶስት ቀናት በሃላ ተመሳሳይ ቃጠሎ ተነስቶ የተዳፈነ እሳት ነው የሚል ምክንያት መሰጠቱ ብዙ ወገኖችን የሚያሳምን አልሆነም፡፡
የቀድሞ የአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ተካ አባዲ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ስራ አስኪያጅ በመሆን ከተሾሙ ካለፉት ሶስትና አራት ወራት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የመንግስታዊዎቹ አዲስዘመንና ኢትዮጽያን ሄራልድ ጋዜጦችን ጨምሮ በተለይ የግል ጋዜጦች ለሕትመት መውጣት ከሚገባቸው ቀናት ቢያንስ ከአንድ እስከ ሶስት ቀናት ዘግይተው በቁዋሚነት እንዲወጡ በመገደዳቸው ለኪሳራ እየተዳረጉ ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡
ይህ ችግር ሁልጊዜም ከማሽኖች እርጅና ጋር የሚያያዝ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተባባሰበት ዋና
ምክንያት አዲሱ ስራ አስኪያጅ በሰፊው ሰራተኞች ዘንድ ተቀባይነት ካለማግኘታቸው ጋር በተያያዘ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የድርጅቱ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በተለይ አዲሱ ስራ አስኪያጅ በቢፒአር ስም ብዛት ያላቸው ሠራተኞችን ለማፈናቀል ማቀዳቸውና ከዚህ በፊት በነበሩበት ማተሚያ ቤት ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዳቸው ሠራተኛው በማስቆጣቱ ነው ተብሎአል፡፡ ቃጠሎውም ከዚሁ ቅሬታ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተገምቶአል፡፡
ማተሚያ ቤቱ በዚህ ከባድ ችግር ውስጥ ሆኖ ከሳምንት በፊት የጋዜጣ አሳታሚ ደንበኞቹን ለስብሰባ በሒልተን ሆቴል በመጥራት ችግሮቹን ለማሻሻል ቃል ቢገባም የሠራተኛው ተነሳሽነት መውደቅ የሕትመት ኢንዱስትሪው ተጨማሪ አደጋ ሆኖአል፡፡ ከሰሞኑ ቃጠሎ ጋር በተያያዘም ወረቀት የለም በሚል የጋዤጦች ሕትመት ሊስተጓጎል ይችላል የሚል ስጋት በብዙ አሳታሚዎች ዘንድ ተፈጥሮአል፡፡
አዲሱ ስራ አስኪያጅ በተሾሙ ማግስት ሰራተኞች ያሰሙትን ተቃውሞ ኢሳት መዘገቡን ተከትሎ፣ ስራ አስኪያጁ መረጃ ያቀበሉ ሰዎችን በማፈላለግ ተጠምደው እንደነበር የውስጥ ምንቾች ተናግረዋል።