ታህሳስ 02 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እግዚአብሄር ለሙሴ ጽፎ የሰጠው የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚገኝበት ቦታ ለሺ አመታት አለምን አነጋግሯል፣ የበርካታ የታሪክ ተመራማሪዎችን ቀልብ ስቦ ቆይቷል፤፡
ታዋቂው ጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ግርሀም ሀንኮክ ከአመታት በፊት ” ዘ ሳይን ኤንድ ዘ ሲል” በሚለው መጽሀፋቸው የቃል ኪዳኑ ታቦት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝ የሚጠቁም መጽሀፍ አሳትመዋል። በመጽሀፋቸውም የካቶሊክ እና የአይሁድ እምነት ተከታዮች አውሮፓውያን ታቦቱን ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መመላለሳቸውን ጠቁመዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የታሪክ ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞችና የሀይማኖት መሪዎች፣ ለቃል ኪዳኑ ታቦት እንደገና ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ መንግስትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታቦቱን ለአለም ህዝብ ይፋ በማድረግ እውነተኛነቱን እንዲያረጋግጡ ግፊት ሲያድረጉ ቆይተዋል፡:
የአለም ህዝብ ትኩረት በታቦቱ ላይ በአረፈበት በአሁኑ ጊዜ፣ አቶ መለስ ዜናዊ፣ ይህን እድል በመጠቀም ታቦቱን ለጉብኝት በማቅረብ ወይም በድብቅ በመሸጥ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለማግኘት አንድ አደገኛ እቅድ መንደፋቸውንም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ምንጮች ገልጠዋል።
በአንትሮፖሎሎጂስቶች ዘንድ ድንቅ የታሪክ ግኝት ተደርጋ የምትቆጠረውና ኢትዮጵያ የሰው ልጆች መገኛ ናት የሚለውን ማእረግ እንድትጎናጸፍ ያስቻለቸው ሉሲ ወይም ድንቅነሽ ፣በአቶ መለስ ዜናዊ ትእዛዝ ወደ አሜሪካ እንድትወጣ መደረጉ ይታወቃል።
ድንቅነሽ ከአገር ስትወጣ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የታሪክ ባለሙያዎች ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ አሰምተዋል።
አቶ መለስ እንደተመኙት ከሉሲ ጉዞ በቂ የሆነ ገንዘብ ሊገኝ አልቻለም። ሉሲን ወደ አሜሪካ ለመላክ የተወሰደው እርምጃ ትልቅ ስህተት እንደነበር የሚያመለክተው የተገኘው ገንዘብ አነስተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ፣ ከእንግዲህ ሉሲ ወደ ኢትዮጵያ አትመለስም የሚለው ስጋት እያየለ በመምጣቱ ጭምር ነው።
የቃል ኪዳኑን ታቦት በተመሳሳይ መልኩ ለኢግዚቢሽን ወይም ለሽያጭ ለማቅረብ እየተወጠነ ያለው ሴራ ኢትዮጵያ በምንም ገንዘብ ሊተመን የማይችለውን ውድ ሀብቷን እንድታጣ ያደርጋታል።
ዲሰምበር 5፣ 2011 ሪክ ዴውስበሪ የተባለ ጋዜጠኛ ሜል ኦንላይን በተባለ ድረገጽ ላይ ” የቃል ኪዳኑን ታቦት የያዘው ቤተክርስቲያን ጣሪያው ማፍሰስ በመጀመሩ የአለም ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ ታቦቱን የማየት እድል ሊገጥመው ይችላል ” ሲል ዘግቦአል።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን የጣሪያውን ማፍሰስ ሳይዘግቡ፣ የውጭ አገር ጋዜጠኛው ሪክ ዳውስበሪ “ያፈሳል” ስለተባለው ህንጻ በፎቶ ግራፍ የተደገፈ ድብቅ ዜና ማቅረቡ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ወገኖች ትኩረታቸውን እንደገና እንዲስቡ አድርጎአቸዋል።
አቡነ ጳውሎስ ፣ በጁን 26፣ 2009 ፣ የሮማ ካቶሊክ መቀመጫ በሆነችው ቫቲካን ከተማ ከፖፕ ቤኔዲክት16ኛ ጋር መገናኘታቸው ተከትሎ አድንክሮኖስ ለተባለው የጣሊያን የዜና ማእከል ” በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰው እግዚአብሄር ለሙሴ የሰጠውንና የእግዚአብሄርን ህግጋት የያዘውን ፣ ለዘመናትም የምርምር እና የጥናት ርእስ ሆኖ የቆየውን፣ የቃልኪዳኑን ታቦት አለም በቅርቡ ያደንቀዋል።” የሚል መግለጫ መስጠታቸው ሰሞኑን “የቤተክርስቲያኑ ጣሪያ በማፍሰሱ አለም እንደገና ታቦቱን የማየት እድል ያገኛል ” ከሚለው ዜና ጋር ተመሳስሎአል።
አቡነ ጳውሎስ “ታቦቱን ለአለም አሳያለሁ” የሚል መግለጫ ከሰጡ በሁዋላ፣ ወዲያውኑ ከምመናን ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው “የጣሊያን መገናኛ ብዙሀን ቃለምልልሴን አዛብተው አቅርበዋል” የሚል ማስተባበያ ሰጥተዋል።
በወቅቱ በቫቲካን ከአቡነ ጳውሎስ ጋር አብረው የተገኙት በጣሊያኖች ዘንድ ጁሊዮ ቢሴሪ በኢትዮጵያኖች ዘንድ ደግሞ ልኡል አክሊለ ብርሀን የተባሉት ባለሀብት እና አሜዲዮ ዲ አኮስታ የተባሉት የጣሊያን ልኡል ናቸው።
በጊዜው የካቶሊክ የሀይማኖት አባቶች የቃል ኪዳኑን ታቦት አይተው ለማረጋገጥ የሚፈቀድላቸው ከሆነ ለአቡነ ጳውሎስ 25 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል እንደተገባላቸው ተዘግቧል።
ገንዘቡ የሚለግሰው “ዳኮስታ ፋውንዴይሽን” በተባለው የኢጣሊያ የኢንዶውመንት ድርጅት በኩል ሲሆን ፣ አቡነ ጳውሎስ ገንዘቡ ” በቫቲካን የሚገኘውን አይነት ሙዚየም በአክሱም ከተማ ለማሰራት ይውላል ብለው” ተናግረው ነበር።
በአቡነ ጳውሎስና በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ባለስልጣናት መካከል እንደ ድልድይ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ደግሞ በኢትዮጵያ ያደጉት ጣሊያናዊው ጁሊዮ ቢሰሪ ወይም አክሊለ ብርሀን መኮንን የሚባሉት ባለሀብት መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። አቡነ ጳውሎስ ከፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ ጋር ሲገናኙ ከአጀቡዋቸው መካከል እኝህ ባለሀብት አንዱ ናቸው።
ጁሊዮ ቢስሪን ወይም አክሊብርሀን መኮንንን ከአቶ መለስ ዜናዊና አዜብ መስፍን ጋር የሚያገናኙት ደግሞ ፣ የአቶ ሳዩም መስፍን የጋብቻ ዘመድ የሆኑት አቶ ቆንስጠንጢኖስ በርሄ ናቸው።
አቶ ቆንስጠንጢኖስ በርሄ ፣ጁሊዮ ቢሴሪ ወይም አክሊብርሀን መኮንን፣ ጊዮን ሆቴልን በ512ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ተስማምተው የመጀመሪያውን 210 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ተስኖአቸው ግዢውን እስካቆሙበት ጊዜ ድረስ የባለሀብቱ የኢትዮጵያ ወኪል ሆነው በኦፊሴል አገልግለዋል።
ቆንስጠንጢኖስ በርሄ አቶ መለስ ዜናዊን ከውጭ አበዳሪ ድርጅቶች፣ ከቻይና ፣ ከህንድ እና ከሌሎችም አገሮች ጋር የሚያገናኙ ሰው መሆናቸው ይነገርላቸዋል።
አቡነ ጳውሎስ ላለፉት ሁለት አመታት ጉዳዩ ትኩረት እንዳይሰጠው አድርገው የቆዩ ሲሆን፣ ሰሞኑን ደግሞ ለቫቲካን ባለስልጣናት የገቡትን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ “የቤተክርስቲያኑ ጣሪያ” ያፈሳል የሚል ሰበብ እንዲነገር ማስደረጋቸውን የውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።
የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚገኝበት ቤተክርስቲያን ጣሪያው ቢያፈስ እንኳን ጉዳዮ በድብቅ ተይዞ ህንጻው እድሳት ይደረግለታል እንጅ ፣ በምንም ተአምር ዜናው ለአለም ህዝብ ሊገለጥ አይገባውም ሲሉ አዋቂዎች ይናገራሉ።
አሁን በጣሪያ ማፍሰስ ሰበብ ፣ የቃል ኪዳኑን ታቦት ለአለም ለማሳየት የሚደረገው ሩጫ በጊዜ ካልተገታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ቤተክርስቲያንን ታሪክ ስር መሰረት ያናጋዋል የሚሉ አስተያየቶችም ቀርበዋል።
አንዳንድ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ግን ታቦቱ ይሸጣል ወይም በቀላሉ ሊንቀሳቀስ ይችላል የሚለውን አባባል አይቀበሉትም።
አቡነ ጳውሎስ ባለፉት 5 አመታት አገር ውስጥ ወደ ሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለጉብኝት ከሄዱበት ይልቅ፣ ወደ ሮም የተመላለሱበት ጊዜ ይበልጣል የሚሉ ምእመናንም ለኢሳት ተናግረዋል።
ጳጳሱ ወደ ጣሊያን በድብቅ በሚመላለሱበት ጊዜ ለእርሳቸው ብቻ የሚቀርቡ ሰዎችን ያስከትላሉ።
ጣሊያን በአለም የማፊያ ወንጀል ስራ ቁጥር አንድ ተጠቃሽ አገር መሆኑዋ፤ የቃል ኪዳኑ ታቦት በአለም ላይ ካሉት እጅግ ውድ ነገሮች ሁሉ ተወዳዳሪ የሌለው በገንዘብ ሊተመን የማይችል ሀብት መሆኑ፤ የአቡነ ጳውሎስ በተደጋጋሚ በድብቅ ወደ ጣሊያን መመላለስ እና አለም በቅርቡ ታቦቱን ይመለከተዋል የሚል መግለጫ መስጠታቸው፤ መለስ ዜናዊ ሉሲን የመሰለ ታሪካዊ ሀብት ለትንሽ ዶላሮች ብለው ወደ ውጭ አገር እንዲወጣ ማድረጋቸውና ለኢትዮጵያውያን ቅርሶች ያላቸው ከበሬታ አነስተኛ መሆን፤ ከዚህ ቀደም በርካታ ውድ የቤተክርስቲያኑዋ እቃዎች፣ ጽላቶችና መስቀሎች በአሜሪካና አውሮፓ ገበያዎች በህገ ወጥ መንገድ መሸጣቸው ፤ ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ኔትወርክ 11 ቢሊዮን ብር በህገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ መውጣቱን መዘገቡ፤ የቆንስጠንጢኖስና የህወሀት ባለስልጣናት የቆየ ግንኙነትና የጁሊዮ ቢሴሪ ወይም አክሊብርሀን መኮንን ግዮን ሆቴልን ለመግዛት ሙከራ ማድረጋቸው እንዲሁም አቡነ ጳውሎስ የተነሳባቸውን ተቃውሞ ተከትሎ ወዲያውኑ ቃላቸውን ማጠፋቸው እና ባለሀብቱ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ጊዮን ሆቴሉን መግዛት አልቻሉም ተብሎ መነገሩ ከሰሞኑ ጣሪያው በማፍሰሱ አለም ታቦቱን የማየት እድል ሊኖረው ይችላል ከሚለው ዜና ጋር ተዛምዶ በቃል ኪዳኑ ታቦት ዙሪያ አንድ ድብቅ ሚስጢር መኖሩን መታዘብ እንደሚያስችል የኢሳት የጥናት ቡድን አመልክቷል።
የቃል ኪዳኑ ታቦት ከእስራኤል ወደ ግብጽ ከዚያም ወደ ጣና ቂርቆስ ገዳም በመጨረሻም በአክሱም ጺዮን ማሪያም እንዲያርፍ መደረጉ ይታወሳል።
በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ገላውድዮስ ከግራኝ ሙሀመድ ጦር ጋር በሚዋጉበት ጊዜ፣ በክርስቶፈር ደጋማ ተመርቶ ንጉሱን ለመርዳት የተላከው የካቶሊክ ሚሲዮናውያን ጦር ድብቅ አላማ የቃል ኪዳኑን ታቦት ፍለጋ እንደነበር የታሪክ መረጃዎች ያሳያሉ።
እንዲሁም ታዋቂውን ተገዥ ተመራማሪ ጀምስ ብሩስን ጨምሮ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በተደጋጋሚ የተጓዙ አሳሾች ዋና ተልእኮዋቸው የቃል ኪዳኑን ታቦት በማጥናት ወደ እየሩሳሌም መመለስ እንደነበር ይነገራል።
ሞሳድ የተባለው የእስራኤል የስለላ ተቋምም ታቦቱን ለመውሰድ በተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። አቡነ ጳውሎስ ታቦቱን በአይናቸው ማየታቸውን መናገራቸው ይታወሳል።
በጉዳዩ ዙሪያ አቡነ ጳውሎስና ልኡል አክሊለ ብርሀን መኮንን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ለወደፊቱ አስተያየታቸውን ስናገኝ እናቀርባለን።