ከቁጫ ጋር በተያያዘ በአርባምንጭ የታሰሩ ከ300 ያላነሱ ሰዎች  ፍትህ አጥተው እየተሰቃዩ ነው

ሰኔ ፭(አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በቁጫ ወረዳ በቅርቡ ከተነሳው የመልካም አስተዳደር፣ የማንነትና የፍትህ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ፍትህ አጥተው ያለፉትን ስምንት ወራት በእስር ቤት ካሳለፉት መካከል አንደኛው ህይወታቸው አልፎአል።

የ14 የቤተሰብ አባላት አስተዳዳሪ የሆኑት የ39 ዓመቱ አቶ ሻልሼ ሸዋ ኮዶ ላዴ ቀበሌ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ ፣ በእስር ቤት ውስጥ ህክማና ተነፍገው  መሞታቸውን የአንድነት ፓርቲ የደቡብ ተወካይ አቶ ዳንኤል ሽበሺ ገልጸዋል።

አቶ ዳንኤል እንደሚሉት አቶ ሻልሼ ምንም አይነት የክስ ቻርጅ ሳይደርሳቸውና የተከሰሱበትንም ጉዳይ በውል ሳያውቁት ችግረኛ ቤተሰቦቻቸውን በትነው ይህን አለም ተሰናብተዋል።

300 ዎቹ እስረኞች በህክምናና አድሎአዊ በሆነ አያያዝ ከፍተኛ የሆነ መጎሳቆል እየደረሰባቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ የአለማቀፍ ኮሚኒቲውና ሌላው ኢትዮጵያዊ እስረኞቹን መርሳቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። ” አሮሞ ሲበደል ሰልፍ ወጥተናል፣ አማራ ሲበደል አውግዘናል፣ አፋር ሲበደል ጮኸናል፣ ነገር ግን 300 የቁጫ ነዋሪ ፍትህ አጥቶ በእስር ቤት መከራውን ሲያይ የሚጮህለት ሰው ማጣቱ አሳዛኝ ነው ” በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በቅርቡ አንድነት ፓርቲ በወረዳው ለያካሂደው የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ መሰረዙንም አቶ ዳንኤል ገልጸዋል። ከአቶ ዳንኤል ሺበሺ ጋር የተደረገው ሙሉ  ቃለምልልስ  ከመጨረሻው ዜና ቀጥሎ ይቀርባል።