የዲላ ነጋዴዎች የስራ ማቆም አድማቸውን ቀጥለዋል

ሰኔ ፭(አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዲላ የሚገኙ ነጋዴዎች ከግብር እና ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር በተያያዘ ላለፉት 3 ቀናት የጀመሩትን ተቃውሞ እንደቀጠሉ ሲሆን፣ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የተሰማሩትም አድማውን እንዲቀላቀሉ ውሳኔ መተላለፉን ነጋዴዎች ገልጸዋል።

የከተማው ከንቲባ አቶ ዮሴፍ ጉሙ መስተዳድሩ የሚያወጣውን መመሪያ ካልተቀበላችሁ አካባቢውን ለቃችሁ መውጣት ትችላላችሁ በማለት በይፋ መናገራቸውን የሚገልጹት ነጋዴዎች፣ ጉዳዩን ለክልሉ ባለስልጣናት ቢያመለክቱም ” ችግሩን እናየዋለን” የሚል መልስ ከማግኘት በስተቀር እስካሁን ለችግራቸው መፍትሄ አላገኙም።

ብዙዎቹ በከተማዋ ያሉ ታላላቅ ባለሃብቶች የመስተዳድሩን ውሳኔ እየተቃወሙት ነው። 6 ነጋዴዎች ከግብር ጋር በተያያዘ ሰሞኑን መታሰራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ አንደኛው ነጋዴ መፈታታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ጉዳዩን በተመለከተ ከንቲባውን ለማግኘት ደጋግመን ብንደውልም ሊሳካልን አልቻለም።