(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 19/2011) ከምዕራብ ጉጂ ዞን ከቀርጫ ወረዳ ተፈናቅለው በይርጋጨፌ የሚገኙት የጌዲዮ ተወላጆች ህይወት አደጋ ውስጥ መውደቁ ተገለጸ።
ኢሳት ከአካባቢው እንዳገኘው መረጃ ከሆነ የተፈናቃዮች ቁጥር 60ሺ ይደርሳል።
ከነዚህ ተፈናቃዮች ከ15ሺ የሚበልጡት ደግሞ በይርጋጨፌ ስታዲየም ውስጥ ያለምንም መግብና መጠጥ ሳምንት ማስቆጠራቸው ነው የተገለጸው።
ተፈናቃዮቹ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች እርዳታ እንዳያገኙ ከመደረጉም በላይ በመከላከያ ሃይል ወደ መጡበት እንዲመለሱ የሚደረገው ማስፈራሪያ ሁኔታዎች አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ምንጮቹ ገልጸዋል።
ከምዕራብ ጉጂ ዞን ከቀርጫ ወረዳ የተፈናቀሉት ቁጥራቸው 60ሺ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በይርጋጨፌ ከተማ ያለምንም እርዳታ እየተሰቃዩ መሆናቸውን ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ የሚያመለክተው።
እነዚህ ተፈናቃዮች አንድ ሙሉ በገጠር በሚገኙ ቀበሌዎች ከነዋሪዎች በሚደረግላቸው እርዳታ ብቻ ቆይተዋል።
ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ከ15ሺ የሚበልጡት ተፈናቃዮች በይርጋጨፌ ከተማ በሚገኘው ስታዲየም ውስጥ በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ነው ከአካባቢው ለኢሳት መረጃውን ያደረሱት ነዋሪዎች የሚናገሩት።
የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለነዚህ ተፈናቃዮች እርዳታ ለማድረግ ቢሞክሩም የአካባቢው ባለስልጣናት እርዳታ የሚፈልግ አካል የለም በማለታቸው በርሃብ እንዲሰቃዩ ተደርገዋል።
ባላስልጣናቱ ይህን እርዳታ ተፈናቃዮቹ እንዳያገኙ የሚያደርጉት ደግሞ በአካባቢው ምንም አይነት ችግር የለም የሚል እሳቤን ለማስፈን ነው ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ግን ተፈናቃዮቹ ምንም አይነት ድጋፍ ኣንዲያገኙ አለመደረጉ የተፈናቃዮቹ ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል።
ከዚህ የከፋው ደግሞ ይላሉ ነዋሪዎቹ ተፈናቃዮቹን ወደ መጣችሁበት ተመለሱ በሚል የሚደረገው ጫና ሁኔታዎቹን የከፉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ተፈናቃዮቹ በተደጋጋሚ ለሚደርስባቸው ወደ መጣችሁበት ተመለሱ ለሚለው ጫና ትላንትም ይህንን ችግር አይተናል ዛሬም የተለየ ነገር ስለሌለ እዚሁ እንሞታለን በሚል ከመከላከያ ሃይሉ ጋር መፋጠጣቸውን ነው የነገሩን።
ወደ መጣችሁበት ተመለሱ በዛ የምግብ እርዳታ ታገኛላችሁ የሚል የማታለያ ቃል ቀርቦላቸዋል ያሉት ነዋሪዎቹ ባለፉት አንድ አመት በዚህ ችግር ውስጥ ሆነው ልርዳችሁ ያላቸው አካል የለም።
በተደጋጋሚ ተፈናቃዮቹ ለሚመለከተው አካል ሁሉ ያቀረቡት የድረሱልን ጥሪም ቢሆን ጆሮ ሰቶ የሚያዳምጥ በመይጥቱ መፍትሄ ማግኘት አልተቻለም ይላሉ ።
ኢሳት ይህን ጉዳይ ይዞ እንደተለመደው ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወዳላቸው አካላት ሁሉ ያደረገ ሙከራ ሊሳካ አልቻለም።