ሐምሌ ፬ ( አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ላፉት አስር እና 20 ዓመታት በመላከያ ግንባሮች በትግል ያሳለፉ እና አካላቸውን አጠው የተመለሱ የኢትዮጵያ መከላከያ አባላት፣ በከፈሉት መስዋዕትነት ምንም አይነት ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆኑ ባህር ዳር በተካሄደው የመከላከያ ተመላሽ አባላት ውይይት ላይ ተናግረዋል።
ከ3 አመታት በፊት ከመከላከያ የተሰናበተ ወታደር፣ “ስንሄድ በከብሮ ተሸኝተን ነበር፣ አሁን ግን ተረስተን በጉስቁልና እየኖርን ነው” በማለት በምሬት ገልጸዋል። 20 አመት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ አገልግያለሁ የሚሉት ወታደር ደግሞ፣ አሁን ታጋይ ነኝ ብሎ የሚያወራ የለም፣ ተቀባይነት የለውም ሲሉ፣ በህዝቡም በገዢው ፓርቲም በኩል ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸዋል። “እኛ አኑዋዋሪዎች ነን እንጅ ነዋሪዎች አይደለንም” በማለት አክለዋል።
በጄ/ል ሳሞራ የኑስ የሚመራው የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮችን ለመቅጠር ተደጋጋሚ ማስታወቂያዎችን በየጊዜው ቢያወጣም የሚፈልገውን ያክል ተመዝጋቢ ሊያገኝ አልቻለም።የተመላሽ ሰራዊት አባላት አዳዲስ ወጣቶች እነሱን እያዩ መከላከያን ሊቀላቀሉ እንደማይችሉ ይገልጻሉ። ከህዝቡም ከመንግስትም ሳንሆን ቀርተናል የሚሉት ወታደሮቹ፣ ህይወታቸውን ለማቆየት በማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ ነው።