ብአዴንን ደግፈን በመታገላቸው እንደሚጸጸቱ የሰቆጣ ነዋሪዎች ተናገሩ

ሐምሌ ፬ ( አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የዋግ ነዋሪዎች በከተሞች ዙሪያ በተጠራ ስብሰባ ላይ ፣ ድርጅቱ በአካባቢያቸው ተመስርቶ አስፈላጊውን ድጋፍ አድርገውለት ለስልጣን ቢያበቁትም፣ ስልጣን ከያዘ በሁዋላ ግን እንደጠላቸውና እንደረሳቸው ተናግረዋል። “አንዳንድ ጊዜ የትግል ታሪካችንን ለመናገር ስንፈልግ፣ የታላላቅ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ታሪክ እንኳን ለመናገር ስንፈልግ፣ የሚያሸማቅቅ ሁኔታ ነው ያለው” በማለት በድርጅቱ እንደሚያፍሩበት ገልጸዋል።
ይህ ህዝብ “ይህንን ድርጅት ደግፎ እዚህ ያደረሰው ጥቅሜን ያስከብርልኛል ብሎ እንጅ መንግስተ ሰማያት ያስገባኛል ብሎ አልነበረም” የሚሉት ነዋሪዎች፣ በአካባቢያቸው የሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እንኳን የሚመለሱላቸው በለቅሶና በቁዘማ” መሆኑን ያስረዳሉ። “ ልብ ያለው ልብ ይበል’ ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።
ብቃት ያለው አመራር የለም ያሉት ሌለው አስተያየት ሰጪ፣ ተሃድሶ ተደረገ ከተባለ በሁዋላ ፣ የተሻሉ የተባሉት ሰዎች ተወግደው ኪራይ ሰብሳቢዎች አሸንፈው ወጥተዋል ይላሉ። “እዚህ ያለው ህብረተሰብ እያለቀሰ፣ ለማን መናገር እንዳለበት ግራ ተጋብቶ የሚገኝ ህዝብ ነው” ሲሉ ያክላሉ።
ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴውን ተከትሎ አገዛዙ “ ጥልቅ ተሃድሶ” በሚል እቅድ ህዝቡን ያረጋጋልኛል በማለት የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስድም፣ ህዝቡ ግን የሚቀበለው አልሆነም።