በኢትዮጵያ 780 ሰዎች በኮሌራ በሽታ መሞታቸው ታወቀ

ሐምሌ ፬ ( አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኮሌራ ወረረሽኝ በኢትዮጵያ አድማሱን እያሰፋ መምጣቱንና በበሽታውም 780 ኢትዮጵያዊያንን መግደሉን ወርልድ ቪዥን በጥናታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል። ከሚያዝያ አጋማሽ እስከ ግንቦት አጋማሽ 2017 እ.ኤ.አ. በተደረገ ጥናት በኢትዮጵያ የኮሌራ ወረሽኝ አድማሱን እያሰፋ ነው።
በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሊያ ክልሎች በአጠቃላይ 567 የነበረው የኮሌራ ተጠቂዎች ቁጥር፣ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ወደ 1 ሺ 80 ጨምሯል።
በአዲሱ ዓመት 2017 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 36 ሺህ 750 የክሌራ በሽተኞች ተመዝገበዋል። ከበሽተኞቹ ከፍተኛውን 61 ከመቶ የሚሸፍነው የሶማሌ ክልል መሆኑንም ጥናቱ አክሎ አመላክቷል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሽታውን ኮሌራ ተብሎ እንዲጠራ አይፈቅድም። የተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች በሽታው ኮሌራ መሆኑን የኢህአዴግ መንግስት እንዲቀበል ተደጋጋሚ ግፊት ቢያደርጉም አልተሳካለቸውም።