ጥቅምት ፬(አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-“ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለማፍረስ ” በሚል ወንጀል የተከሰሰው እውቁ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ከተባለ በሁዋላ፣ ውሳኔውን በእስር ላይ ሆኖ እንዲሰማ ፍርድ ቤት ባዘዘው
መሰረት ወደ እስር ቤት ተልኳል።
ጋዜጠኛ ተመስገን የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ሲሰራ ” ድህረ ምርጫ 1997 ዓምን ተከትሎ ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ በተደረገው የአደባባይ አመጽ እንዲሁም በአረብና በሰሜን አፍሪካ የተከሰቱ የህዝብ ዓመጽ በሃገራችን እንዲተገበር
በማሰብ ወጣቶች በአደባባይ ለአመጽ እንዲወጡ በጽሁፉ መቀስቀሱን፣ ህዝቡ በሀገሪቱ መንግስትና በህገመንግስታዊ ስርዓቱ እንዲያምጽ እንዲሁም ስርአቱ እንዲፈርስ በጋዜጣው አማካኝነት የቀሰቀሰ በመሆኑ በፈጸመው የመገፋፋትና ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር
ወንጀል ” መከሰሱ በክስ ቻርጁ ላይ ተመልክቷል።
ተመስገን የቀረበበትን ክስ ሲያስተባብል ቢቆይም ፍርድ ቤት ግን ጥፋተኛ ብሎታል። የተከሰሰባቸው አንቀጾች ተመስገንን የረጅም ጊዜ እስር ሊያስወስኑበት ይችላል።
ተመስገን በሚጽፋቸው ጽሁፎች የበርካታ አንባቢያንን ቀልብ የገዛና ና ብዙ ተካዮች ያሉት ጋዜጠኛ ሲሆን ፍትህ ጋዜጣን ጨምሮ እርሱ የሚሰራባቸው የተለያዩ መጽሄቶች እንዲዘጉ ሲደርግ ቆይቷል።
መንግስት በሰበብ አስባቡ ጋዜጠኞችን በጸረ ሽብር ህጉ እየከሰሰ ወህኒ ማውረዱ አለማቀፍ ትችት እያስከተለበት ነው። በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ርእዮት አለሙና ውብሸት ታየ የተለያዩ አለማቀፍ ሽልማቶች አሸናፊ መሆናቸው ይታወቃል።
በሌላ ዜና ደግሞ የማራኪ መፅሔት ባለቤት እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር የነበረው ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤ በስደት በሚኖርበት ናይሮቢ ኬኒያ ሰኞ ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በድንገት ህይወቱ አልፏል፡፡ ጋዜጠኛ ሚሊዮን መንግስት በቅርቡ የከፈተውን ክስ ተከትሎ
ከአገር መሰደዱ ይታወቃል።