እስራኤል በሶሪያ ያለውን የኢራን ወታደራዊ ተቋም ማፈራረሱዋን ገለጸች

እስራኤል በሶሪያ ያለውን የኢራን ወታደራዊ ተቋም ማፈራረሱዋን ገለጸች
(ኢሳት ዜና ግንቦት 02 ቀን 2010 ዓ/ም) የአገሪቱ መንግስት እንደገለጸው ኢራን በጎላን ተራራ አካባቢ የሮኬት ጥይቶችን መተኮሷን ተከትሎ እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ሶሪያ ውስጥ የሚገኘው የኢራን ወታደራዊ ሰፈር እንዲወድም አድርጋለች።
እስራኤል የኢራን አብዮታዊ ዘቦች 20 ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሳቸውን ገልጻለች ። ይህንን ተከትሎ የኢራንን የጦር መሳሪያዎች ማከማቻ፣ ወታደራ ቁሳቁስ ማጠራቀሚያ፣ የነዳጅ ማደያ እና የስለላ ጣቢያዎችን ማውደሟን እስራኤል አስታውቃለች ።
ኢራን እስካሁን የሰጠችው መግለጫ ባይኖርም ፣ የሶሪያ መንግስት የአገሪቱ መከላከያ በርካታ የእስራኤል ሚሳኤሎችን በአየር ላይ ማምከኑን አስታውቋል ። ይሁን እንጅ የተወሰኑ ሚሳኤሎች የተለያዩ ወታደራዊ ጣቢያዎች ፣ ራዳሮችንና የጦር ማከማቻዎችን ማውደማቸውን የሶሪያ መንግስት አምኗል።
ኢራን ለበሸር አላሳድ መንግስት ድጋፏንት ሰጣለች። እስራኤል በበኩሏ ኢራን ሶሪያ ውስጥ የምታደርገውን ማንኛውንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደማትታገስ ታስጠነቅቃለች። የአሁኑ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አካባቢውን ወደ ጦርነት ሊቀይረው ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።
አሜሪካ ራሷን ከኢራን የኒዩክሊየር ስምምነት ባወጣች ማግስት የተወሰደው የእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ፣ እስራኤል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራፕ አሜሪካን ከኒውክለየር ስምምነቱ እንዲያወጡ ጫና አሳድራባቸዋለች የሚለው መላምት ክብደት እንዲያገኝ አድርጎታል።