(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 13/2011)የኢትዮጵያ ስፓርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ /ኤስ ኤፍ ኤን ኤ/ በአንድ የቀድሞ የቦርድ አባሉ ቀርቦበት የነበረውን ክስ በድል ማጠናቀቁን ለኢሳት በላከው መግለጫ አስታወቀ።
አስፋው ተፈሪ የተባለ የቀድሞ የፌዴሬሽኑ ቦርድ አመራር አባል ከሀላፌነቴ ያለአግባበ ተነስቻለሁ በሚል በፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ ክርክሩን በማሸነፉ 100 ሺ የአሜሪካን ዶላር በፌዴሬሽኑ እንዲከፈለው አስወስኖ ገንዘቡም ተከፍሎት ቆይቷል።
ይህ በሆነበት ጊዜም ፌዴሬሽኑ ወሳኔውን በመቃወም የሰጠውን መግለጫ መነሻ በማድረግ አስፋው ተፈሪ ስሜ ጠፍቷል በሚል እንደገና ሌላ ክስ አቅርቦ ነበር ።
ፌዴሬሽኑ ለጉዳዩ ተኩረት በመስጠት ደምሴ ኤንድ ቸርች የተባለ የህግ ተቋም በመቅጠር በጉዳዩ ላይ ከተከራከረ በኋላ በካሊፎርኒያ ከፍተኛ የችሎት ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ ውድቅ እንዲሆን አስደርጎታል ። በዚህ ውሳኔም አስፋው ተፈሪ ለፌዴረሽኑ የጠበቃና የህግ ወጭውን 24 ሺህ 51 ዶላር እንዲከፍል ትዛዝ ተሰጥቷል።
በዚህ ወሳኔ ያልተደሰተው አስፋው ተፈሪም እንደገና ይግባኝ ቢጠይቅም ወሳኔው ስለጸናበት ተጨማሪ የጠበቃና የህግ ወጭ እንዲከፍል በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ተወስኖበታል።
የፌዴረሽኑ ጠበቃ አቶ ደረጀ ደምሴ ለኢሳት በሰጡት መግለጫ አስፋው ተፈሪ በፍርድ ቤቱ ወሳኔ መሰረት ለጠበቃና ለሕግ ወጭ በጠቅላላው ከ80 ሺህ ዶላር በላይ ሊከፍል ይችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜርካ በቀድሞ የቦርድ አባሉ የቀረበበትን ክስ ማሸነፉ ለአስፋው ተፈሪም ሆነ ለመሰሎቹ ጥሩ ትምሀርት እንደሚሰጥ ፌዴሬሽኑ ለኢሳት በላከው መግለጫ አስታውቋል።