በራያ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ወከባና እንግልት እየተባባሰ መምጣቱ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 13/2011)በራያ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ወከባና እንግልት እየተባባሰ መምጣቱን የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ አግዘው ህዳሩ አስታወቁ።

በተለይ ወጣቶች በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ የሚደረገው አፈናና ድብደባ እየተባባሰ መቷል ብለዋል።

ፋይል

ስቃይና እንግልቱ የበዛበት እንድ የራያ ወጣትም ራሱን ማጥፋቱ ታውቋል።

የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄን ለማስመለስ የተለያዩ ስራዎችን ቢሰራም በራያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት ግን ሊቆም አልቻለም ይላሉ የኮሚቴው ሊቀመንበር አቶ አግዘው ህዳሩ።

በራያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ካለው ስቃይ ጋር በተያያዘም እስካሁን 31 ሰዎች ተገድለዋል፣ከ1ሺ 9 መቶ በላይ ሰዎች ታስረዋል፣31 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ አሁን ላይ በቀረውና ማንም በማይከሰስበት የሽብር ህግ ተከሰው ስቃያቸውን እየተቀበሉ ይገኛሉ ብለዋል።

ከዚህ የከፋው ደግሞ ሁኔታው አስመርሯቸው አካባቢውን ለቀው የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ ነው ይላሉ።

እንደ እሳቸው አባባል ከሆነ በተለይ ሰሞኑን በራያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት እየተጠናከረ መቷል።–ከምሽት ሁለት ሰአት ጀምሮ ባጃጅ የሚሰሩ ወጣቶች እንዳይንቀሳቀሱ በማገድም ጭምር።

በተለይ በወጣቱ ላይ ልዩ ሃይሉ እያደረሰ ያለው ስቃይ እየከፋ ነው ይላሉ አቶ አግዘው።–ወጣቶችን ከማሰር እስከመደብደብ ያለውን ተግባር በማሳያነት በማቅረብ።

በየጊዜው እየደረሰበት ያለው ዛቻና እንግልት ከአቅሙ በላይ የሆነበት አንድ ወጣትም ራሱን ለማጥፋት መገደዱን ተናግረዋል።

ወጣቱ መረጃ ታቀብላለህ በሚል ሰበብ ከስራ እናባርርሃለን፣እናስርሃለንና እንገልሃለንን የመሳሰሉ ዛቻዎች እየበዙ በመምጣታቸውንና ያንን መቋቋም ባለመቻሉ ራሱን አጥፍቷል ብለዋል።

በአካባቢው የመከላከያ ሃይል ቢኖርም ልዩ ሃይሉ በራያ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት ግን ማስቆም አልቻለም ይላሉ።

ተወላጆቹ ልዩ ሃይሉ እያደረሰባቸው ያለውን ስቃይና እንግልት የመከላከያ ሃይሉ እንዲከላከልላቸው ቢጠይቁም ከመከላከያ ሃይሉ የተሰጣቸው ምላሽ እኔ የመጣሁት መንገድ ልጠብቅ እንጂ እናንተ ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለመከላከል አይደለም ሲል ምላሽ መስጠቱ ታውቋል።

አቶ አግዘው እንደሚሉት የድንበርና የማንነት ኮሚሽን መቋቋሙ እኛ የምናነሳውን ችግር ሊፈታ ይችል ይሆናል።

ነገር ግን የተሰየመው ኮሚሽን መፍትሄ እስኪያመጣ ድረስ ህብረተሰቡ በነጻነት ተንቀሳቅሶ መብቱን እንዲጠይቅ አለመደረጉ ግን ዋጋ እያስከፈለ ነው ብለዋል።