(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 26/2011) በኢትዮጵያና በኤርትራ መሀል የተደረሰውን የሰላም ስምምነትና አወንታዊ እርምጃዎችን ለማደናቀፍ ቱርክ ከምታደርገው እንቅስቃሴ እንድትቆጠብ ኤርትራ አሳሰበች።
የኤርትራ ሙስሊም ሊግ የሚል ድርጅት በመፍጠርም ሉዋላዊነቴን የሚጋፋ ድርጊት ቱርክ ፈጽማብናለች ስትልም ኤርትራ ክስ አቅርባለች።
ኳታርና ሱዳን ደግሞ በተባባሪነት ከሚያካሂዱት ድርጊት እንዲታቀቡም የኤርትራ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወታው መግለጫ አሳስቧል።
በኤርትራ በኩል የቀረበውን ክስ በተመለከተ ስማቸው ከተጠቀሱት ሀገራት የተሰጠ ማስተባቢያም ሆነ ማረጋገጫ የለም።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ይፋዊ ገጽ ላይ በወጣው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ኤኬፒ በሚል በሚጠራው ገዢ ፓርቲ የሚመራው የቱርክ መንግስት የኤርትራን ሉአላዊነትና ጥቅም የሚነኩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው።
ሻባት የተሰኘው የኤርትራ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ድረገጽ የኤርትራን መንግስት ስልጣን የሚጋፋ ድርጊት በሚል የተገለጸው ክስ ላይ እንደጠቀሰው ቱርክ የኤርትራ ሙስሊም ሊግ የተሰኘ ንቅናቄ ጽሕፈት ቤት በሱዳን መክፈቷ ኤርትራን አስቆጥቷል።
በቱርክ መንግስት ድጋፍ ያለው ይህ ንቅናቄ በቅርቡ በካርቱም ባደረገው ስብሰባ ኤርትራንና ኢትዮጵያን የሚያወግዙ መልዕክቶችን ማውጣቱን የገለጸው የኤርትራ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ መግለጪያ የቱርክ ድርጊት የኤርትራን ሉአላዊነት የሚዳፈር ነው ሲል ያትታል።
ኤርትራ እንዳለችውም የቱርክ ትንኮሳ እየተባባሰ የመጣው በተለይ ኤርትራና ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።
በሁለቱ ሃገራት መሀል የተደረገው እርቅና በጎ ለውጦችን ለመቀልበስና ለማደፍረስ የቱርክ መንግስት ትንኮሳውን ማጠናከሩን ነው በኤርትራ በኩል የተገለጸው።
የቱርክ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያንና የኤርትራን መልካም ግንኙነት በማወክ አልቆመም ያለችው ኤርትራ በአጠቃላይም የአፍሪካውን ቀንድ ቀውስ ውስጥ ለመክተት በቱርክ በኩል ትንኮሳ እንዳለም አስታውቃለች።
ኤርትራ ከቱርክ ሌላ ኳታርንና ሱዳን ላይ ክስ ማቅረቧን ሻባት ዘግቧል።
ኳታር በቱርክ በኩል የሚካሄደውን የትንኮሳ ተግባር በገንዘብ ድጋፍ ትሰጣለች የተባለች ሲሆን ሱዳን መሬቷን ለዚሁ ተግባር በመፍቀድ ክስ ቀርቦባታል።
በዚህ ዓመት በይፋ እንቅስቃሴውን ለጀመረውና በቱርክ መንግስት ለሚደገፈው የኤርትራ ሙስሊም ሊግ ጽሕፈት ቤት እንዲኖረው በማድረግና እንዲንቀሳቀስ በመፍቀድ ነው ሱዳን በኤርትራ የተወቀሰችው።
የኤርትራ መንግስት በቱርክ በኩል እየተካሄደ ነው ያለው የትንኮሳ ተግባር ውጤት አይኖረውም ስትልም አጣጥላለች።
በካርቱም ጽሕፈት ቤት የከፈተው የኤርትራ ሙስሊም ሊግ የሚያደርገው እንቅስቃሴም ባዶ ጩኽት እንጂ ተጽዕኖ አያመጣብኝም ብላለች ኤርትራ።
ቱርክ በኤርትራ መንግስት የቀረበባትን ውንጀላ በተመለከተ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም። ኳታርና ሱዳንም ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጡም።
በኤርትራ መንግስት መግለጫ ስሟ የተጠቀሰው ኢትዮጵያም በጉዳዩ ላይ የሰጠችው አስተያየት የለም።