የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ ሆነ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 26/2011) በቅርቡ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ሲበር የተከሰከሰው የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከአብራሪዎች ውጭ በሆነ ችግር መሆኑን የምርመራው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት አመለከተ።

የምርመራ ቡድኑ ባወጣው የመጀመሪያ የምርመራ ሪፖርት  የአውሮፕላኑ አብራሪዎች በአምራቹ ቦይንግም ሆነ በአሜሪካ የፌዴራል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተቀመጡ መስፈርቶችን ያሟሉ እንደነበሩ አረጋግጧል።

የመርማሪ ቡድኑ በአውሮፕላን አደጋው ቅድመ ሪፖርቱ አራት ነጥቦችን ያካተተ ሁለት የደህንነት ምክረ ሐሳቦችንም አቅርቧል፡፡

የምርመራ ቡድኑ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት  አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲጓዝ  መብረር የሚያስችለው የፀና ሠርተፍኬት ያለው እንደነበርና አብራሪዎቹም ይኼንን በረራ ለማድረግ የሚያስችላቸው ብቃትና ተገቢው የበረራ ፈቃድ ነበራቸው ብሏል፡፡

አውሮፕላኑ ለበረራ ሲነሳ በትክክለኛ መስመርና ለመብረር የሚያስችለው ሁኔታ ላይ እንደነበር በሪፖርቱ ተጠቁሟል።

አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ በአምራቹ የተሰጠውን የበረራ ቅደም ተከተል አብራሪዎቹ  በተደጋጋሚ ለመቆጣጠር ቢሞክሩም እንዳልቻሉም ነው የገለጸው።

አውሮፕላኑ በሰላም ተንደርድሮ የተነሳ እንደነበርም የመርማሪ ቡድኑ መሪዎችና አባሎች፣ ገልጸዋል።

በረራው ከተጀመረ በኋላም አውሮፕላኑ የአፍንጫ መደፈቅ ሲያሳይና አብራሪዎቹም ለመቆጣጠር ሲሞክሩ እንደነበር ሆኖም ግን ሊቆጣጠሩት ባለመቻላቸው መከስከሱን የምርመራ ቡድኑ አስታውቋል፡፡

የአደጋ ምርመራ ቡድኑ በአደጋው ወቅት አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር የሚያስቸግረውን የአውሮፕላኑን የፊተኛውን ጫፍ ወይም አፍንጫ የመደፈቅ ችግር ተጋልጧል ብሏል።

እናም አምራቹ በበረራ ወቅት አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን የበረራ ቁጥጥር ሥርዓቱን እንዲፈትሸው ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

አምራቹ አደጋው የደረሰበትን አውሮፕላን ወደ በረራ ከመመለሱ በፊት የሚመለከታቸው የአቪዬሽን ባለሥልጣናትና ተቋማት ችግሩን የሚያስወግድ የበረራ ቁጥጥር ሥርዓት በበቂ ሁኔታ መዘርጋቱን ሊያረጋግጡ ይገባልም ሲል ምክሩን ሰጥቷል፡፡

ከአውሮፕላኑ የመረጃ ሳጥን የተገኘው መረጃም ከውጭ አካል በአውሮፕላኑ ላይ የደረሰበት ጥቃት እንደሌለም አረጋግጧል ተብሏል፡፡

የአደጋው ሙሉ ሪፖርት በዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ እንደሚወጣ የምርመራ ቡድኑ አስታውቋል፡፡