ኢትዮጵያ ሆቴል እንዲፈርስ የተላለፈው ውሳኔ ተቃውሞ ገጠመው

ግንቦት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ኢትዮጵያ ሆቴልና ከጎኑ የሚገኘው  የበጎ አድራጎት ሕንፃ ፈርሰው፣ በቦታው ላይ 60 ፎቅ ያለው ሆቴል እንዲገነባ የተወሰነው ውሳኔ ተቃውሞ ገጥሞታል ሲል የዘገበው ሪፖርተር ነው።

ተቃውሞውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ያቀረቡት ከ 81 ዓመት በፊት በተገነባውና  አሁን ከ ኢትኦጵያ ሆቴል ጋር እንዲፈርስ በተወሰነበት በፖላስሪያቴሪ በጎ አድራጎት ሕንፃ ላይ የሚኖሩ ነጋዴዎች ናቸው፡፡

ነጋዴዎቹ ተቃውሟቸውን ለከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ያቀረቡ ቢሆንም፣ እስካሁን ምላሽ ባለማግኘታቸው አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

በቅርቡ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ሆቴልን ለመሸጥ ያወጣውን ጨረታ “በላይነህ ክንዴ ኢምፖርት ኤክስፖርት ኩባንያ” አሸንፎ ሆቴሉን እንደተረከበ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ኩባንያው ታሪካዊውን ኢትዮጵያ ሆቴልን የገዛው በ94 ሚሊዮን ብር ነው።

ኩባንያው ከዚህም ባሻገር  ለአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ተጨማሪ የማስፋፊያ መሬት በሊዝ እንዲሰጠው በጠየቀው መሠረት ካቢኔው በጉዳዩ ላይ ከመከረ በኋላ “የሚገነባው ግዙፍ ሆቴል የከተማውን ውበት ወደ ተሻለ ደረጃ ከሚያሸጋግሩ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው” በሚል 1,700 ካሬ ሜትር ተጨማሪ መሬት ፈቅዶለታል።

በዚህ ለኩባንያው በተጨመረለት መሬት ላይ ከሚገኙት ነባር ግንባታዎች መካከል ፦ አሁን በኗሪዎቹ እንዳይፈርስ ተማፅኖ የቀረበበት የበጉ አድራጎቱ ሕንፃ አንዱ ነው፡፡

“በዚህ ሕንፃ ለአርባ ዓመታት ስንሠራ ኖረናል”የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች ፣ ሕንፃው ቅርስ ሆኖ ሊመዘገብና ሊጠበቅ እንደሚገበወም ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ሕንፃ ጋር በተመሳሳይ ደረጃ የሚገኙት ብሔራዊ ቴአትርና መከላከያ ሚኒስቴር ያሉባቸው ሕንፃዎች በቅርስነት መመዝገባቸውን ያወሱት ነጋዴዎቹ ሕንፃው ለአካባቢው ውበትን ከማላበሱ በተጨማሪ በርካቶች የዕለት ጉርሳቸውን የሚያገኙባቸው ንግድ ቤቶች ያሉበት በመሆኑ፣ መንግሥት ውሳኔውን ሊያጤነው ይገባል የሚል መከራከርያ ያቀርባሉ፡፡

ተቃውሞ በማቅረብ ላይ የሚገኙት ነጋዴዎች ያቋቋሙትን ኮሚቴ የሚሰበስቡት የሺሕ ሰለሞን ኃይሉ ሱፐርማርኬት ባለቤት አቶ ሞገስ ኃይሉ ፣ እሳቸውና ተቃውሞ አቅራቢዎቹ በቦታው ላይ ግንባታ ለማካሄድ ጥያቄ ማቅረብ ያልደፈሩት ሕንፃው ቅርስ ነው በሚል ምክንያት እንደነበር ለጋዜጣው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት እንደ ቅርስ ሳይታይ ለሌላ አልሚ መወሰኑ አግባብ አለመሆኑንና ልማት መካሄድ ካለበትም ከኢትዮጵያ ሆቴል ባለቤት ጋር በጋራ ማልማት እንዲፈቅድላቸው አቶ ሞገስ አበክረው ጠይቀዋል፡፡

ይሁንና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት አስተዳደር ነጋዴዎቹ- በሦስት ወራት ጊዜ ሕንፃውን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን አቶ ሞገስ አጥብቀው ተቃውመዋል፡፡

“በላይነህ ክንዴ ኢምፖርት ኤክስፖርት ኩባንያ”ም፤ ኢትዮጵያ  ሆቴልንና  የበጉ አድራጎት ሕንፃ በማፍረስ ከፍታው 60 ፎቅ የሆነ ዘመናዊ ሆቴል ለማስገንባት እንቅስቃሴውን ቀጥሏል፡፡

የኩባንያው ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው -“ የእኔ ሐሳብ ለአገሬ አንድ የሚታይ ጥሩ ነገር ለመሥራት እንጂ ሌላ ዕቅድ የለኝም፤ ለተነሺዎችም ክፉ አልመኝም” ይላሉ፡፡

በላይነህ ክንዴ በየዓመቱ ሰሊጥን፣ቡናን እና የቁም ከብትን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን የሚልክ ኩባንያ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የደረቅ ጭነት አገልግሎትና የኮንስትራክሽን መሣርያዎች ኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎችን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ በቅርቡ ፀሐይ ኢንዱስትሪ የሚባለው ኩባንያው- በቃሊቲ ብረታ ብረትና በፀሐይ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከፍተኛ አክሲዮን ባለቤት ሆኗል፡፡

የአገር ቅርስ የነበረው ጣይቱ ሆቴል ከ ዓመታት በፊት ለስርዓቱ ቅርበት ለነበራቸው ሰዎች በዝቅተኛ ዋጋ መሸጡ ይታወሳል።

በአሁኑ ጊዜ የበጎ አድራጎት ሕንፃ እንዲፈርስ በመወሰኑ ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ያሉት ነጋዴዎች፤ መንግሥት አቤቱታቸውን ሰምቶ ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጣቸው እየጠየቁ ነው፡፡