የመንግስት ባለስልጣናት በፈጠሩት ችግር በአፋርና በአማራ ድንበሮች ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሮ ሰዎች ተገደሉ

ግንቦት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- በሰሜን ሸዋ ዞን በቀወት ወረዳ በአፋር እና በአማራ ተወላጆች መካከል በመንግስት ባለስልጣናት በተቀሰቀሰ ችግር ባለፉት 2 ወራት ብቻ ከ15 ያላነሱ ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋል፣ ከብቶችም ተዘርፈዋል። ከአካባቢው ነዋሪዎች የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ባለፈው ሀሙስ እና አርብ በተፈጠረው ግጭት አንድ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሎ ሌላ አንድ ሰው ደግሞ ቆስሏል። ግጭቱን የፈጠሩት የታጠቁ የአፋር ተወላጆች ሲሆኑ፣ የቀወት ነዋሪዎች ራሳቸውን ለመከላከል ባደረጉት ጥረት ከአፋርም ከአማራም ሰዎች ተገድለዋል። ከአለፈው አርብ ጀምሮ የፌደራል ፖሊስ አካባቢውን የተቆጣጠረ ቢሆንም፣ የአካባቢው ሰዎች ቀያቸውን እየለቀቁ በመሄድ ላይ ናቸው።

ግጭቱን የፈጠሩት የአፋር ክልል የህሙሮበ ገለአሎ አካባቢ ባለስልጣናት ከስልጣን መባረራቸውን ተከትሎ የአካባቢያቸውን ሰዎች አስታጥቀው ጥቃት እንዲፈጽሙ ማድረጋቸውን ግጭቱ የተፈጠረበት የግልጥበረት እና የቀቢቻ ጎጥ አካባቢዎች ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አየለ ግፋው ለኢሳት ገልጸዋል።

ህዝቡ ሆነ በአካባቢው ያሉት ባለስልጣናት መንግስት ችግሩን ለመፍታት ባለመሞከሩ ቅሬታ እያደረበት መምጣቱን ሊቀመንበሩ አክለው ገልጸዋል።

መንግስት ችግሩን ለመፍታት እንዴት ሊሳነው ቻለ በሚል ለቀረበላቸው ባለስልጣኑ “ለእኛም ለአመራሮቹ ጥያቄ የሆነብን ይህ ነው፣ መንግስት ሁሉንም ብሄር በአንድ አይን አይቶ አመራር የሚሰጥ ቢሆን ችግሩ ይፈታ ነበር ”  በማለት መልሰዋል።

ከሊቀመንበሩ ጋር ያደረግነውን  ቃለምልልስ ሙሉውን በሰሞኑ ዝግጅት እንደምናቀርብ ለመግለጽ እንወዳለን።

የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ሰሞኑን ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት በክልሎች የሚታዩ ግጭቶች እየቀነሱ መምጣታቸውን ተናግረው ነበር። ለኢሳት የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ከጎሳ ጋር የተያያዙ ግጭቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ነው።