ኢትዮጵያውያን በኢንጂነር ስመኛው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን እየገለጹ ነው
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 20 ቀን 2010 ዓ/ም ) በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች በአባይ ግድብ ዋና መሃንዲስ በኢንጂነር ስመኛው ሞት የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ፣ የኢንጂኒሩ አሟሟት ሁኔታ በፍጥነት ተጣርቶ ለህዝብ እንዲገለጽ እየጠየቁ ነው።
በጎንደር ከተማ ወጣቶች ወደ አደባባይ ወጥተው ተቃውሞአቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ የከተማው የአገር ሽማግሌዎች ወጣቶችን በመምከር አረጋግተዋቸዋል። በባህርዳርና በደሴ እንዲሁ የከተማዋ ነዋሪዎች የሻማ ማብራት ስነስርዓት በማድረግ ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
የኢንጂነር ስመኜው በቀለን ሞት ተከትሎ በቁጣ ወደ አደባባይ ከወጡት የጎንደር ወጣቶች መካከል አንድ የ14 ዓመት ታዳጊና አንድ ሌላ ወጣት በጥይት ተመተዋል።
ለኢሳት የድረሰው በምስል የተደገፈ መረጃ እንደሚያመለክተው በዛሬው ዕለት በጎንደር ለተጠራውን ሰልፍ ኃላፊነት የወሰደ የሚታወቅ አካል የለም።
ይህም በመሆኑ በርካታ አክቲቪስቶች ከትናንት ምሽት ጀምሮ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሰልፉ እንዳይደረግ እና ወጣቱ ከቁጣ ስሜት በመውጣት ነገሮችን በስክነትና በጥንቃቄ እንዲከታተል ሲጠይቁ ውለዋል።
በጥይት የተመቱት ወጣቶች ወደ ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እየተከታተሉ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በብ አዴኑ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በአቶ ተስፋዬ እና በኢንጂነር ስመኜው ሞት ሀዘናቸውን የገለጹት የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ፣ወጣቱ ከግብታዊ የቁጣ እንቅስቃሴ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ኃላፊው አቶ ንጉሡ ጥላሁን “በተቀደደልን የጥፋት ቦይ ልንፈስ አይገባም !!” በሚል ርዕሰ ባሰፈሩት ጽሁፍ -“ጠቅላይ ሚኒስትራችን “መግደል መሸነፍ ነው እንዳሉት” ተሸናፊዎች ስመኛውን ገድለውታል፡፡ ገዳዮች ልብ ያላሉት ነገር ቢኖር፤ ኢንጅነር ስመኛውን በመግደል መላ ኢትዮጵያውንን ማሸነፍ አለመቻቸውን ነው”ብለዋል።
“ገዳዮቹ የጀመርነውን ለውጥ መቀልበስ የማይቻላቸው መሆኑንም አልተገነዘቡትም፡”ያሉት አቶ ንጉሡ፤ “ ለውጡ ሊቀለበስ የሚችለው እነሱ በቀደዱልን የጥፋት ቦይ ስንፈስ መሆኑን በመገንዘብ መንገዳችንን የሳትን እንስተካከል”ሲሉ መክረዋል።
አክለውም፦” ክልልችንን የነውጥ ፤የግርግር እና የሁካታ ክልል በማድረግ ለውጡ እውን እዳይሆን ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ስለሆነ መንቃት ይገባናል”ብለዋል።
መንግስት ባወጣው መግለጫ ደግሞ የተጀመረው ተስፋ ሰጪ ጉዞ በማንኛውም ጊዜ ፈተናዎች ሊያጋጥሙት እንደሚችል መገንዘብ የሚገባ ሲሆን፣ አንዳች ፈተና ባጋጠመን ቁጥር በስሜታዊነት የምንወስዳቸው እርምጃዎች ዞረው የለውጡን ጥልቀትና ስፋት እንዳይገድቡ እና እንዳያደናቅፉት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል ብሏል። “የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ፣ በትዕግስትና በጽናት እየተቋቋምን ከያዝነው ዓላማ ዝንፍ ሳንል በጋራ እየፈታን ማለፍ ይገባናል ሲል” አክሏል።
“የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አፈጻጸም በአሁኑ ወቅት የሚገኝበትን ደረጃ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማሳወቅ ጋዜጠኞችን በአካል ቦታው ድረስ ወስደው በተጨባጭ ለማሳየት በዝግጅት ላይ እያሉ” መሞታቸው መሰማቱን የገለጸው መንግስት፣ ስለአሟሟታቸው ሁኔታ በዝርዝር ለማወቅ የተጠናከረ የወንጀል ምርመራ በመካሄድ ላይ መሆኑን ፣ ምርመራው ተጠናቆ ውጤቱ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆን አስታውቋል።