ኢህአዴግ ግንቦት 20ን የአባይን ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር ሊያከብር ነው

ግንቦት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ኢህአዴግ አዲስአበባን የተቆጣጠረበትን 22ኛ ዓመት ክብረበአል የአባይን ግድብ አቅጣጫ በማስቀየር ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆኑን የኢህአዴግ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

ስነስርዓቱ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በጉባ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በሚገኙበት እንደሚካሄድ ታውቋል። ኢህአዴግ የወንዙን አቅጣጫ በማስቀየር የኢትዮጵያን ህዝብ በእለቱ ለማስደመም ማቀዱን ለማወቅ ተችሎአል።

የወንዙን አቅጣጫ የማስቀየር ሥራ ክንውን አስመልክቶም የፊታችን ሰኞ ግንቦት 19/2005 ዓ.ም ከ10:30 ጀምሮ በብሔራዊ ቲአትር የሙዚቃዊ ድራማ ዝግጅት መዘጋጀቱም ታውቋል፡፡

የወንዙን አቅጣጫ የማስቀየሩ ስራ የፊታችን ማክሰኞ ቢካሄድም መንግስት አጠቃላይ ግንባታው በተያዘለት እቅድ መሰረት ለመከናወን እንደማይችል ፍንጭ ሰጥቷል።

ከአማራ ክልል መንግስት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የመንግስት ሰራተኞች ለአባይ ግድብ መዋጮ አንዲከፍሉ የተጠየቁትን ገንዘብ ከ90 በመቶ በላይ የከፈሉ ሲሆን ፣ የክልሉ ነጋዴዎች ደግሞ 1 ቢሊዮን ብር እንዲከፍሉ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ለመሰብሰብ የተቻለው 16 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው። መንግስት ገንዘቡን በሚቀጥሉት አስር አመታት ለመሰብሰብ ማቀዱንም ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

ከተጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘውና የግንባታው ስራ ከ11 በመቶ በላይ ተጠናቋል የተባለው የዚህ ግድብ መገንባት በሌሎች የተፋሰሱ አባል አገራት በተለይም ስምምነታቸውን በይፋ ባልገለጹት ግብጽና ሱዳን ላይ ተጽዕኖ ማምጣት አለማምጣቱን ከአንድ ዓመት በላይ ሲመረምር የቆየው ዓለምአቀፍ የኤክስፐርቶች ቡድን ሪፖርቱን በዚህ ወር ያቀርባል
ተብሎ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት የግድቡ ሥራ ትልቁ አካል የሆነው የአባይን ወንዝ አቅጣጫ የማስቀየር ሥራ መገባቱ አነጋጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡

በቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በጎ ፈቃድ የተመሰረተው ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶቹ ቡድን የሚያቀርበው ሪፖርት ለኢትዮጽያ የማይጠቅም ከሆነ በግብጽና ሱዳን ብቻም ሳይሆን በተፋሰሰ አባል አገራት ጭምር የታየው ትብብር መሰረቱን ሊያናጋው እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ሥጋታቸውን በተደጋጋሚ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጽያ በበኩሏ ጥናቱ ሌሎች አገራት እንደማይጎዳ ማረጋገጫ አገኝበታለሁ በማለት ተስፋ የጣለች ሲሆን ይህ ባይሆንም ግን ከግንባታው የሚያግደኝ አይኖርም ስትል በተደጋጋሚ መናገሯ የጥናቱን ውጤት የምትቀበለው አስከጠቀማት ብቻ መሆኑ ግን ሌላ ዙር ቀውስ ውስጥ እንዳይከታት ተሰግቷል፡፡

97 በመቶው የግብርና ምርቱን በአባይ ውሃ ላይ ጥገኛ ያደረገችው ግብፅ ከግድቡ መገንባት ጋር በተያያዘ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ አሉታዊ የሆነ ተፅዕኖን ሊፈጥር ይችላል በሚል ሥጋቷን በተለያየ መንገድ ስትገልፅ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ በአንፃሩ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት ከመጉዳት ይልቅ እንዲውም ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በተደጋጋሚ ስትገልፅ ቆይታለች። በኢትዮጵያ በኩል ግድቡ የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ባልተጠበቀ ጐርፍ እንዳይጥለቀለቁ፣ ግድቦቻቸው በደለል እንደይሞላና የወሃ ትነቱንም
ለመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው  ሲገለፅ ቆይቷል። ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በተለይ ግብፅና ሱዳን በግድቡ ግንባታ ላይ ሥጋት ካላቸው አጠቃላይ የግድቡን ሁኔታ የሚመረምር የኤክስፐርቶች ቡድን ተቋቁሞ የራሱን ሞያዊ ሪፖርት እንዲያቀርብ ፈቃደኝነቷን ገልፃለች።

በዚህም መሠረት International Panel of Experts በሚል አንድ ቡድን ተቋቁሞ በህዳሴው የግንባታ ቦታ በመገኘት የራሱን ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። ቡድኑ ስድስት አባላትን ያቀፈና ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅና ከሱዳን ሁለት ሁለት ኤክስፐርቶችን አካቷል፡፡ ከዚህ ውጪም አራት ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶችን እንዲይዝ የተደረገ ነው። የኤክሰፐርት ቡድኑ ባለፈው ኣመት ግንቦት ወር ላይ የመጀመሪያውን ጉብኝት በግድቡ አካባቢ በመገኘት ያደረገ
ሲሆን፤ የመጀመሪያ ስብሰባውንም በሰኔ ወር 2004 ላይ አድርጓል። ቡድኑ በያዝነው ግንቦት ወር 2005 ዓ.ም የመጨረሻ የግድቡን የአንድምታ ተፅዕኖ ጥናቱን ውጤት ለሦስቱም መንግሰታት የሚያቀርብ መሆኑን ገልጿል።