የኡራዔል አካባቢ ነጋዴዎች ሱቆቻቸው ከታሸጉ አራት ወራት መቁጠሩን ተናገሩ

ግንቦት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ በተለምዶ ኡራኤል ተብሎ በሚጠራው ቂርቆስ ክፍለከተማ በአሁኑ አጠራር ወረዳ 8 የንግድ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነጋዴዎች የመስሪያ ቦታቸውን ሕይወት ብርሃን ለተባለ ቤተክርስቲያን በአስቸኳይ ለቀው እንዲያስረክቡ መገደዳቸውን ባለመቀበላቸው ሱቆቻቸው በክፍለከተማው ከታሸጉ አራት ወራት እንደሞላው በምሬት ገለጹ፡፡

በአካባቢው የኮንስትራክሽን የፋብሪካ ውጤቶች በችርቻሮና በጅምላ የሚቀርብበትና ከፍተኛ ግብር ከፋይ የንግዱ ኀብረተሰብ አባላትን ያቀፈ አካባቢ ነው። በየካቲት ወር አጋማሽ ግን የስራ ጊዜያቸውን እያጠናቀቁ የሚገኙት የወረዳው የስራ ኃላፊዎች ከአቶ ኩማ ደመቅሳ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ለማስፈጸም ሲሉ አካባቢው ለልማት ስለሚፈለግ በአምስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ነጋዴዎች ከቦታቸው እንዲነሱ ማስገደዳቸውና ነጋዴዎቹም እምቢተኛ በመሆናቸው ሱቆቹን አሽገው መሄዳቸው ታውቋል፡፡

ቦታው ለልማት ሲፈለግ በቦታው ላይ ያሉ ሰፋሪዎች ሕግና ሥርዓቱን በጠበቀ መልክ ቢያንስ የዘጠና ቀናት የጊዜ ገደብ ሰጥቶ፣ ለግል ቤቶች ተገቢውን ካሳ ተከፍሎአቸው መነሳታቸው ተገቢ አሰራር ቢሆንም የቂርቆስ ክፍለከተማ ውሳኔ ግን ይህን ሕግና ሥርዓትን ያልተከተለ መሆኑ ነጋዴዎቹንና በስራቸው የሚተዳደሩ ሰዎችን አሳዝኗል፡፡