በደሴ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በፌደራል ፖሊሶች ተደበደቡ

ግንቦት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዘወትር አርብ የጁመዓን ስግደት ተከትሎ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ” ድምጻችን ይሰማ” በማለት የሚያቀርቡት ተቃውሞ ከአዲስ አበባ ውጭ የተካሄደ ሲሆን  በደሴ ሸዋ በር መስጂድ የተካሄደው ተቃውሞ በጸጥታ ሀይሎች እንዲበተን ተደርጓል። የፌደራል ፖሊስ አባላት በወሰዱት እርምጃም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶች ተደብድበዋል። አንዳንድ ወጣቶች በጽኑ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶችም ታፍሰው በመኪና ተጭነው መወሰዳቸውን የአይን ምስክሮች ለኢሳት ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የደሴ ከተማ ከንቲባን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በሻሸመኔ ፣ በጅማ እና በአጋሮ የተደረጉት ተቃውሞች በሰላም መጠናቀቃቸውን የአነጋገርናቸው ሙስሊሞች ገልጸዋል።

ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ድምጻችን ይሰማ በማለት ከአመት በፊት ያቀረቡት የመብት ጥያቄ ዛሬም አልተፈታም። መንግስት የድምጻችን ይሰማ አመራር አካላትን አስሮ በሽብርተኝነት ወንጀል እንደከሰሳቸው ይታወቃል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሀሙስ እለት ባወጣው መግለጫ በእስር ላይ በሚገኙት የሙስሊም መሪዎች ላይ አሰቃቂ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው አመልክቷል።