ኢህአዴግ “ገምግሞ ከስልጣን ያወረዳቸውን ባለስልጣናት” ወደ ትምህርት ሊልክ ነው

ታኅሣሥ ፲፰ (አሥራ ስምንት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ በጥልቅ ትሃድሶ ስም  በሙስና የተዘፈቁ ያላቸውን 479 የአማራ እና የኦሮምያ ክልሎች የወረዳ እና የቀበሌ ባለስልጣናት ወደ ትምህርት ሊላከቸው መሆኑን ምንጮች ገለጹ።

“ኢህአዴግ ህዝብን ያስቸገሩ እና ያመረሩ ፣ የመልካም አሰተዳደር ችግር ያለባቸው እና ስርአቱን አደጋ ውስጥ የጣሉ ናቸው” በሚል ከአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች የተለዩትን ባለስልጣናት ማባረሩ “አመራሮቹ ወደ ተቃዋሚዎች ገብተው ለስርዓቱ አደጋ ይፈጥራሉ”በሚል ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መወሰኑን ምንጮች ይገልጻሉ። “አመራሩን ገሎ ፓርቲውን ማዳን” በሚለው መርህ የተለዩት እነዚህ የኦህዴድና ብአዴን ባለስልጣናት፣ ለቅጣት የሚያበቃ በቂ ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል ተብሎአል።

ህዝብን ለማስደሰት ሲባል አመራሮችን ከስልጣናቸው በማንሳት በየሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ለሶስት አመታት በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ባለስልጣናቱ የቀድሞ ደሞዛቸው እና ጥቅማ ጥቅሞቻቸው  እንደተከበሩላቸው በመረጡት የትምህርት መስክ ገብተው እንዲማሩ እና በይፋ ከህዝብ ፊት ይቅርታ አቅርበው ከስልጣናቸው መውረዳቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ በሚሰሩበት መስሪያ ቤት እና በህዝብ ማስታወቂያዎች ሰሌዳዎች እንዲለጠፍ ድርጅቱ ውሳኔ አሳልፏል።

ገዥ ፓርቲ ኢህአዴግ በከፍተኛ ግምገማ ህዝብን በመመዝበር በሙስና እና ስርዓቱን በዝህብ ዘንድ  እንዲጠላ አድርገውብኛል  ያላቸውን 319 አመራሮች ለህዝቡ በጥፋታቸው ከኃላፊነታቸው ወርደዋል የሚለውን ደብዳቤ እና ስያሜ በመስጠት በሁለተኛ ዲግሪ በሲቪል ሰርቪስ እና በመለስ አመራር አካዳሚ የሁተኛ ዲግሪ ወይም ማስተርስ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ያደረጋል፡፡

በዚህ ከጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት አማካሪዎች በወጣው እና አቶ ሃይለማርያም ባጸደቁት  እቅድ መሰረት 138 ባለስልጣናት ያላቸው ዲፕሎማ በመሆኑ በመጀመሪያ ዲግሪ በመረጡት የትምህርት መስክ ከ2009 ክረምት ጀምሮ የሚላኩ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ በተማሩት ተዘማጅ የትምህርት መስኮች እንዲማሩ እንደጥፋታቸው መጠን የትምህርት እድገት መስጠቱን ለኦሆዴድ እና ለበአዴን በላከው የትዕዛዝ መልዕክት አስታውቋል፡፡

እነዚህን አመራሮች ወደ እስር ቤት መክተት ሲገባ የትምህርት እድል በመስጠት መልሶ አዘጋጅቶ ለመሾም የሚሄድበት አሰራር ድርጅቱ ጥልቅ ተሃድሶ በማለት የጀመረው እንቅስቃሴ የይስሙላ መሆኑን ያሳያል ሲሉ የመጀረጃው ምንጮች ይገልጻሉ።

በከፍተኛና መካከለኛ አመራሩ ላይ ምንም እርምጃ ሳይወሰድ ዝቅተኛ አመራሩ ላይ የተወሰደው እርምጃ፣ ኢህአዴግ ራሱን ለመለወጥ እንደማይችል የሚያመልክት በመሆኑ ህዝቡ ለሙሉ ስርዓት ለውጥ የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል እነዚሁ የድርጅቱ አባላት ይመክራሉ።