ኢህአዴግ ከ700 በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ሰብስቦ ቅስቀሳ አደረገ

መጋቢት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-ትናንት ሀሙስ መጋቢት 12 ቀን 2005 ዓም የኢህአዴግ መንግስት ከ740 በላይ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎችን ስድስት ኪሎ በሚገኘው ስብሰባ ማእከል ለአንድ ሙሉ ቀን በመሰብሰብ በመጪው የአዲስ አበባና አካባቢ ምርጫ ኢህአዴግን እንዲመርጡ ቀስቅሷል።

ለእያንዳንዱ ተሳታፊ 100 ብር ከመስጠት በተጨማሪ  የምሳ፣ የቡና እና የሻሂ ግብዣም አድርጓል።

የጎዳና ተዳዳሪዎች ትናንት 2፡30 ላይ ነጭ ቲሸርት ለብሰው እና  የኢህአዴግ አርማ ያለበት የወረቅት ኮፍያ አድርገው ወደ ስብሰባው አዳራሽ የገቡ ሲሆን፣ በስብሰባው ላይ  ኢህአዴግ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ካለፉት መንግስታት በተሻለ እንደሚያስብላቸው፣ የሙያ ስልጠና ሲሰጣቸው መቆየቱን እና በዚህም እንቅስቃሴ ለቁም ነገር የበቁ የጎዳና ተዳዳሪዎች መኖራቸውን ገልጿል።

የጎዳና ተዳዳሪዎችን ማሰልጠንና በአንድ አካባቢ አሰባስቦ የማኖር እቅድ እንዳለውም ኢህአዴግ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ገልጿል። አንዳንድ የጎዳና ተዳዳሪዎች ” በምርጫ ተሳትፈን ስለማናውቅ እንዴት እንደምንመርጥ አናውቅም ፣ ቀኑንም አናውቅም፣ ማንን እንደምንመርጥም አናውቅም ” በማለት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ “መቼ እና ማንን እንደምትመርጡ እኛ እናሰለጥናችሁዋለን፣ እናሳውቃችሁዋለን፣ ኢህአዴግን ከመርጣችሁ ችግሮቻችሁ ይፈታሉ” በማለት መድረኩን ይመሩ የነበሩ ባለስልጣናት መልሰዋል።

አንድንድ የጎዳና ተዳዳሪዎች ምንም አይነት ቋሚ አድራሻ እና የቀበሌ መታወቂያ እንደሌላቸው የገለጹ ሲሆን ፣ ሰብሳቢው እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ተወክለው የመጡት የፖሊስ ባልደረባ ” ችግር የለም ስማችሁን በትክክል አስፍሩ እንጅ በአቅራቢያችሁ በሚገኙ ቀበሌዎች የመታወቂያ ወረቅት ይዘጋጅላችሁዋል ፣ ፎቶም ትነሳላችሁ “የሚል መልስ ሰጠተዋቸዋል።

በእረፍት ሰአት ወጣቶች የተሰጣቸውን የታሸገ ውሀ በሲጋራ ሲለውጡ እና በርካሽ ዋጋ ሲሸጡ መታዘቡን ዘጋቢያችን ገልጿል።
በቅርቡ በሚካሄደው የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫ 33 የፖለቲካ ድርጅቶች ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል። “አስገራሚው ነገር” ይላል ዘጋቢያችን ሪፖርቱን ሲያጠቃልል፣  “የምርጫ ካርድ የመውሰጃ ጊዜ  እንዳለፈ ከተነገረ ከወራት በሁዋላ የጎዳና ተዳዳሪዎች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱና እንደሚርጡ አሁንም እየተቀሰቀሱ ነው።”

ኢህአዴግ በ2002 ዓም ለተደረገው ብሄራዊ ምርጫ   52 ሚሊዮን ብር ማውጣቱን መዘገባችን ይታወሳል።